መደምደሚያ
‘በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን የምትኮርጁ ሁኑ።’—ዕብራውያን 6:12
1, 2. በዛሬው ጊዜ እምነት ማዳበራችን ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።
እምነት። ይህ ቃል አንድን ግሩም ባሕርይ የሚያመለክት ነው። ይሁን እንጂ ይህን ቃል ስንሰማ አጣዳፊነቱም ሊታወሰን ይገባል! ምክንያቱም እምነት ከሌለን ባፋጣኝ ይህን ባሕርይ ማዳበር ይኖርብናል። እምነት ካለን ደግሞ እንዳይጠፋ ልንጠብቀውና ይበልጥ ልናዳብረው ይገባል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
2 አንድን ጭልጥ ያለ በረሃ እያቋረጥክ እንዳለህ አድርገህ አስብ። በውኃ ጥም ተቃጥለሃል። በዚህ ወቅት ጥቂት ውኃ ብታገኝ ተንኖ እንዳያልቅብህ ከፀሐይ ትከልለዋለህ። እንዲሁም ያሰብክበት ቦታ እስክትደርስ ድረስ ውኃው እንዳያልቅ ባገኘኸው አጋጣሚ ሁሉ የጎደለብህን መልሰህ ለመሙላት ጥረት ታደርጋለህ። በዛሬው ጊዜም የምንኖረው እውነተኛ እምነት ልክ እንደ ውኃው ብርቅ በሆነበት እንዲሁም ካልጠበቅነውና መልሰን ካልሞላነው በቀላሉ ተንኖ ሊጠፋ በሚችልበት በመንፈሳዊ በረሃ በሆነ ዓለም ውስጥ ነው። በመሆኑም እምነት ማዳበራችን ወሳኝ ነው፤ ምክንያቱም ካለ ውኃ መኖር እንደማንችል ሁሉ ያለ እምነትም በመንፈሳዊ ሕያው ሆነን መቀጠል አንችልም።—ሮም 1:17
3. ይሖዋ እምነታችንን ለመገንባት የሚረዳን ምን ዝግጅት አድርጎልናል? ልንዘነጋቸው የማይገቡ ሁለት ቁም ነገሮች ምንድን ናቸው?
3 ይሖዋ እምነት ማዳበራችን ምን ያህል አጣዳፊ እንደሆነ ያውቃል፤ እንዲሁም ይህን ባሕርይ ማዳበርም ሆነ ጠብቆ መኖር በጣም አስቸጋሪ መሆኑን ይረዳል። እምነት በማሳየት ረገድ ምሳሌ የሚሆኑን ሰዎች ታሪክ እንዲሰፍርልን ያደረገው ለዚህ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ሐዋርያው ጳውሎስ በይሖዋ መንፈስ ተመርቶ ‘በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን የምትኮርጁ ሁኑ’ በማለት ጽፏል። (ዕብ. 6:12) የይሖዋ ድርጅት በዚህ መጽሐፍ ላይ እንደተጠቀሱት ያሉ ታማኝ የሆኑ ወንዶችና ሴቶች የተዉትን ምሳሌ ለመከተል ከፍተኛ ጥረት እንድናደርግ የሚያበረታታን ለዚህ ነው። ታዲያ አሁን ከእኛ የሚጠበቀው ምንድን ነው? የሚከተሉትን ሁለት ቁም ነገሮች መዘንጋት የለብንም፦ (1) ምንጊዜም እምነታችንን ማጠናከር ያስፈልገናል፤ (2) ምንጊዜም ተስፋችን እውን ሆኖ ሊታየን ይገባል።
4. ሰይጣን የእምነት ጠላት መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? ይሁንና ተስፋ መቁረጥ የሌለብን ለምንድን ነው?
4 ምንጊዜም እምነትህን አጠናክር። እምነት ኃይለኛ ጠላት አለው፤ እሱም ሰይጣን ነው። የዚህ ዓለም ገዢ ይህን ሥርዓት እምነትን ጠብቆ ለመኖር አስቸጋሪ የሆነ በረሃ አድርጎታል። ሰይጣን ከእኛ የላቀ ኃይል አለው። ታዲያ እንዲህ ሲባል እምነት ማዳበርም ሆነ ይህን ባሕርይ ጠብቆ መኖር አይቻልም ማለት ነው? በፍጹም! ይሖዋ እውነተኛ እምነት ለማዳበር ለሚጥሩ ሁሉ ጥሩ ወዳጅ ነው። እሱ ከጎናችን እስካልተለየ ድረስ ዲያብሎስን መቃወም አልፎ ተርፎም ከእኛ እንዲሸሽ ማድረግ እንደምንችል ማረጋገጫ ሰጥቶናል! (ያዕ. 4:7) በየዕለቱ ጊዜ መድበን እምነታችንን በማጠናከርና በመገንባት ሰይጣንን መቃወም እንችላለን። ይሁን እንጂ ይህን ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል?
5. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ታማኝ የሆኑ ወንዶችና ሴቶች እምነት ማዳበር የቻሉት እንዴት ነው? አብራራ።
ገላ. 5:22, 23) ይሖዋ የእሱን እርዳታ ለማግኘት ያቀረቡትን ልመና ሰምቶ እምነታቸውን አጠናክሮላቸዋል። እኛም ይሖዋ፣ መንፈሱን እንዲሰጣቸው ለሚለምኑና ከጸሎታቸው ጋር የሚስማማ እርምጃ ለሚወስዱ ሁሉ መንፈሱን በልግስና እንደሚሰጥ ባለመዘንጋት የእነሱን አርዓያ እንከተል። (ሉቃስ 11:13) ሌላስ ማድረግ የምንችለው ነገር ይኖራል?
5 ቀደም ብለን እንደተመለከትነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ታማኝ የሆኑ ወንዶችና ሴቶች ይህን ባሕርይ ይዘው አልተወለዱም። እነዚህ ሰዎች እምነት የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ የሚያፈራው ባሕርይ እንደሆነ የሚያሳዩ ሕያው ማስረጃዎች ናቸው። (6. ከምናነበው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
6 የላቀ እምነት ካሳዩት የይሖዋ አገልጋዮች መካከል በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። በዚህ ረገድ ምሳሌ ሊሆኑን የሚችሉ እጅግ ብዙ የአምላክ አገልጋዮች አሉ! (ዕብራውያን 11:32ን አንብብ።) እያንዳንዳቸው በተዉት ምሳሌ ላይ ጸሎት የታከለበት ጥልቅ ምርምር ልናደርግ እንችላለን። ታማኝ ስለሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች የሰፈሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ላይ ላዩን የምናነብ ከሆነ እምነታችን ሊጠናከር አይችልም። ከምናነበው ነገር የተሟላ ጥቅም ለማግኘት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባውን አውድና ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን መረጃዎች ጊዜ ወስደን በጥልቀት መመርመር ይኖርብናል። እነዚህ ፍጽምና የጎደላቸው ወንዶችና ሴቶች “እንደ እኛው ዓይነት ስሜት” ያላቸው መሆኑን ምንጊዜም የምናስታውስ ከሆነ የተዉልንን ምሳሌ መከተል ይበልጥ ቀላል ይሆንልናል። (ያዕ. 5:17) እኛ የገጠመን ዓይነት ተፈታታኝና አስቸጋሪ ሁኔታ ባጋጠማቸው ወቅት ምን ተሰምቷቸው ሊሆን እንደሚችል መረዳት አያዳግተንም።
7-9. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች እኛ ዛሬ ይሖዋን በምናመልክበት መንገድ እሱን ማምለክ ቢችሉ ኖሮ ምን ሊሰማቸው ይችል ነበር? (ለ) ያወቅነውን ነገር በተግባር በማዋል እምነታችንን ይበልጥ ማጠናከር ያለብን ለምንድን ነው?
7 በተጨማሪም ያወቅነውን ነገር ተግባራዊ በማድረግ እምነታችንን ማጠናከር እንችላለን። ደግሞም ‘እምነት ያለ ሥራ የሞተ ነው።’ (ያዕ. 2:26) ታሪካቸውን ስንመረምር የቆየነው ወንዶችና ሴቶች በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ እንድናከናውነው የሰጠንን ሥራ እንዲሠሩ ቢጠየቁ ኖሮ ምን ያህል ይደሰቱ እንደነበር አስብ!
8 ለምሳሌ ያህል፣ አብርሃም በምድረ በዳ በቆመ የድንጋይ መሠዊያ ላይ ለይሖዋ አምልኮ ከማቅረብ ይልቅ “ከሩቅ” ያያቸው ተስፋዎች በዝርዝር በሚብራሩባቸው ማራኪ የሆኑ የመንግሥት አዳራሾችና ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተው አምላክን በተደራጀ መልክ ከሚያመልኩ የአምላክ ሕዝቦች ጋር በመሆን ይሖዋን ማምለክ እንደሚችል ቢነገረው ምን ይሰማው ነበር? (ዕብራውያን 11:13ን አንብብ።) ኤልያስስ ቢሆን ክፉና ከሃዲ በሆነው ንጉሥ የግዛት ዘመን ውስጥ ይሖዋን ለማገልገል ሲጥር ክፉ የሆኑትን የበኣል ነቢያት ከማስገደል ይልቅ አጽናኝና ተስፋ ሰጪ የሆነ መልእክት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለሰዎች እንዲያደርስ ቢጠየቅ ኖሮ ምን ይሰማው ነበር? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ታማኝ ወንዶችና ሴቶች እኛ ዛሬ ይሖዋን በምናመልክበት መንገድ የማምለክ አጋጣሚ ቢያገኙ ምንኛ ደስ ባላቸው ነበር!
9 ስለዚህ ያወቅነውን ነገር በተግባር በማዋል እምነታችንን ይበልጥ እናጠናክር። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ
በመንፈስ መሪነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ የተጠቀሱት የእምነት ሰዎች የተዉትን ምሳሌ ተግባራዊ አድርገናል ሊባል ይችላል። እንዲሁም በዚህ መጽሐፍ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው እነዚህ የእምነት ሰዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የቅርብ ወዳጆቻችን እንደሆኑ ይሰማናል። እንዲያውም በቅርቡ ከእነዚህ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ጋር ይበልጥ የምንቀራረብበት አጋጣሚ እናገኛለን።10. በገነት ውስጥ ምን አስደሳች ሁኔታ ይጠብቀናል?
10 ተስፋህ እውን ሆኖ ይታይህ። ታማኝ የነበሩ ወንዶችና ሴቶች ሁሉ አምላክ ከሰጣቸው ተስፋ ማበረታቻ አግኝተዋል። አንተስ? ለምሳሌ ታማኝ የሆኑ የአምላክ አገልጋዮች ‘ጻድቃን ከሞት በሚነሱበት’ ጊዜ ዳግም ሕያው ሲሆኑ ከእነሱ ጋር መገናኘት ምን ያህል እንደሚያስደስት አስብ። (የሐዋርያት ሥራ 24:15ን አንብብ።) እነዚህን ሰዎች መጠየቅ የምትፈልጋቸው አንዳንድ ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?
11, 12. በአዲሱ ዓለም (ሀ) አቤልን፣ (ለ) ኖኅን፣ (ሐ) አብርሃምን፣ (መ) ሩትን፣ (ሠ) አቢግያንና (ረ) አስቴርን ምን ጥያቄዎች ልትጠይቃቸው ትችላለህ?
11 አቤልን ስታገኘው ወላጆቹ ምን ይመስሉ እንደነበር ለመጠየቅ ትጓጓለህ? ወይም ደግሞ እንዲህ ብለህ ልትጠይቀው አስበህ ይሆናል፦ “ወደ ኤደን የሚወስደውን መንገድ ይጠብቁ የነበሩትን ኪሩቦች ለማነጋገር ሞክረህ ነበር? ምን ምላሽ ሰጡህ?” ኖኅንስ ስታገኘው ምን ብለህ ልትጠይቀው ትፈልጋለህ? ምናልባት እንዲህ ልትለው ትፈልግ ይሆናል፦ “ኔፊሊሞችን ስታይ ፈርተህ ነበር? በመርከብ ውስጥ በነበራችሁበት ጊዜ እነዚያን ሁሉ እንስሳት መመገብ የቻልከው እንዴት ነው?” አብርሃምን ስታገኘው ደግሞ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ታስብ ይሆናል፦ “ሴምን በአካል አግኝተኸው ታውቃለህ? ስለ ይሖዋ የነገረህ ማን ነው? ዑርን ለቆ መውጣት ከብዶህ ነበር?”
12 በተመሳሳይም ከሞት የሚነሱትን ታማኝ ሴቶች መጠየቅ የምትፈልጋቸውን አንዳንድ ጥያቄዎች አስብ። “ሩት፣ ይሖዋን ለማምለክ ያነሳሳሽ ምንድን ነው?” “አቢግያ፣ ለዳዊት ያደረግሽውን ነገር ለናባል መንገር ፈርተሽ ነበር?” “አስቴር፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከሰፈረው ዘገባ በኋላ አንቺና መርዶክዮስ እንዴት ሆናችሁ?”
13. (ሀ) ከሞት የሚነሱት ሰዎች ምን ጥያቄዎችን ሊጠይቁህ ይችላሉ? (ለ) በጥንት ዘመን ይኖሩ ከነበሩት ታማኝ የሆኑ ወንዶችና ሴቶች ጋር ስለመገናኘት ስታስብ ምን ይሰማሃል?
13 እርግጥ ነው፣ እነዚህ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች አንተንም ብዙ ጥያቄዎች ሊጠይቁህ ይችላሉ። በመጨረሻዎቹ ቀናት መደምደሚያ ላይ ስለተከናወኑት ነገሮችና ይሖዋ በአስቸጋሪ ጊዜያት ሕዝቦቹን እንዴት እንደረዳቸው ለእነሱ መንገር በጣም አስደሳች ነው! ይሖዋ የሰጣቸውን ተስፋዎች በሙሉ ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ ያደረገው እንዴት እንደሆነ ሲሰሙ በአድናቆት እንደሚዋጡ ጥርጥር የለውም። በአዲሱ ዓለም ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱት የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች በአእምሯችን ለመሳል መሞከር አይጠበቅብንም። ምክንያቱም በገነት ውስጥ አብረውን ይኖራሉ! ስለሆነም አሁን እነዚህ ሰዎች እውን ሆነው እንዲታዩህ የቻልከውን ያህል ጥረት ማድረግህን ቀጥል። በእምነታቸው ምሰላቸው። የቅርብ ወዳጆችህ ከሆኑት ከእነዚህ ታማኝ ሰዎች ጋር ለዘላለም ይሖዋን በደስታ እንድታገለግል እንመኝልሃለን!