ምዕራፍ ሁለት
“ከእውነተኛው አምላክ ጋር ይሄድ ነበር”
1, 2. ኖኅና ቤተሰቡ በምን ሥራ ተጠምደው ነበር? ያጋጠሟቸው አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎችስ ምንድን ናቸው?
ኖኅ ከወገቡ ቀና ካለ በኋላ የዛሉትን ጡንቻዎቹን ለማፍታታት ሰውነቱን አሳሳበ። ከሥራው አረፍ በማለት በአንድ ትልቅ ግንድ ላይ ተቀምጦ ግዙፍ የሆነውን የመርከቡን መዋቅር ሲመለከት በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ትኩስ ከሆነው ቅጥራን የሚወጣው የሚሰነፍጥ ሽታ አካባቢውን አናውጦታል፤ ለእንጨት ሥራ የሚያገለግሉት መሣሪያዎች የሚፈጥሩት ድምፅ ያስተጋባል። ኖኅ አረፍ ካለበት ቦታ ሆኖ ልጆቹ የመርከቡን የተለያዩ እንጨቶች ለማገጣጠም ደፋ ቀና ሲሉ ይመለከታል። ልጆቹ፣ የልጆቹ ሚስቶችና ውድ ባለቤቱ በዚህ የግንባታ ሥራ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ከእሱ ጋር ሲደክሙ ቆይተዋል። ምንም እንኳ ብዙ ሥራ ያከናወኑ ቢሆንም ከፊታቸው ገና ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል!
2 የአካባቢው ሰዎች ኖኅንና ቤተሰቡን የሚመለከቷቸው ሞኞች እንደሆኑ አድርገው ነው። የመርከቡ ሥራ እየገፋ በሄደ መጠን የአካባቢው ሰዎችም የዚያኑ ያህል ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ ይመጣል በሚለው ሐሳብ ይሳለቁ ነበር። ኖኅ ጥፋት እንደሚመጣ በተደጋጋሚ ቢነግራቸውም እነሱ ግን ይህ ማስጠንቀቂያ ከእውነታው የራቀና ሊታመን የማይችል እንደሆነ ተሰምቷቸዋል! አንድ ሰው እንዲህ ባለ የሞኝነት ድርጊት እንዴት የራሱንም ሆነ የቤተሰቡን ሕይወት በከንቱ ያባክናል ብለው ሳይገረሙ አይቀሩም። ይሁን እንጂ የኖኅ አምላክ የሆነው ይሖዋ ይህን ሰው የሚመለከተው ከዚህ ፈጽሞ በተለየ መንገድ ነው።
3. ኖኅ ከአምላክ ጋር ሄዷል ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?
3 የአምላክ ቃል “ኖኅ ከእውነተኛው አምላክ ጋር ይሄድ ነበር” ይላል። (ዘፍጥረት 6:9ን በNW አንብብ። *) ይህ ምን ማለት ነው? ይህ አባባል አምላክ በምድር ላይ መሄዱን ወይም ኖኅ በሆነ መልኩ ወደ ሰማይ መውጣቱን የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኖኅና ይሖዋ ልክ እንደ ጓደኛሞች አብረው እንደተጓዙ ተደርጎ የተቆጠረው ኖኅ አምላኩን በጥብቅ ይታዘዝና ከልብ ይወድ ስለነበረ ነው። በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኖኅ ሲናገር ‘በእምነቱ አማካኝነት ዓለምን ኮነነ’ ብሏል። (ዕብ. 11:7) ይህ የሆነው እንዴት ነው? እኛስ ኖኅ ካሳየው እምነት ምን ልንማር እንችላለን?
በጠማማ ዓለም ውስጥ እንከን የለሽ ሆኖ የኖረ ሰው
4, 5. በኖኅ ዘመን በዓለም ላይ ክፋት ከዕለት ወደ ዕለት እየባሰ የሄደው እንዴት ነው?
4 ኖኅ ያደገው ከዕለት ወደ ዕለት በክፋት እየባሰ ይሄድ በነበረ ዓለም ውስጥ ነው። ከአምላክ ጋር እንደሄደ የተነገረለት ሌላው ጻድቅ ሰው ይኸውም የኖኅ ቅድመ አያት ዘፍ. 5:22፤ 6:11፤ ይሁዳ 14, 15) ለመሆኑ በምድር ላይ ያለው ሁኔታ እንዲባባስ ያደረገው ነገር ምንድን ነው?
የሆነው ሄኖክ በኖረበት ዘመንም ክፋት ተስፋፍቶ ነበር። ሄኖክ በዓለም ላይ የነበሩትን ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች አምላክ እንደሚፈርድባቸው ትንቢት ተናግሮ ነበር። በኖኅ ዘመን ደግሞ ክፋት ይበልጥ ተባብሶ ነበር። እንዲያውም ምድር በዓመፅ በመሞላቷ የተነሳ በይሖዋ ፊት ረክሳ ነበር። (5 የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች በሆኑት መላእክት መካከል በጣም አሳዛኝ የሆነ ነገር ተከስቶ ነበር። ቀድሞውንም ቢሆን ከመካከላቸው አንዱ በይሖዋ ላይ ያመፀ ሲሆን አምላክን በመሳደብና አዳምንና ሔዋንን አታልሎ ኃጢአት እንዲሠሩ በማድረግ ሰይጣን ዲያብሎስ ሆኖ ነበር። በኖኅ ዘመን ደግሞ ሌሎች መላእክትም በይሖዋ የጽድቅ አገዛዝ ላይ ማመፅ ጀመሩ። አምላክ በሰማይ የሰጣቸውን ቦታ ትተው ወደ ምድር በመምጣት ሥጋዊ አካል ከለበሱ በኋላ ከሰው ልጆች መካከል ውብ የሆኑ ሴቶችን አገቡ። ትዕቢተኛና ራስ ወዳድ የሆኑት እነዚህ ዓመፀኛ መላእክት በሰው ልጆች ላይ መጥፎ ተጽዕኖ አሳድረዋል።—ዘፍ. 6:1, 2፤ ይሁዳ 6, 7
6. ኔፊሊሞች በዓለም ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድረው ነበር? ይሖዋስ ምን ለማድረግ ወሰነ?
6 በተጨማሪም ሥጋ የለበሱት መላእክትና የሰዎች ሴቶች ልጆች ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ ሁኔታ በመጣመራቸው የተነሳ እጅግ ግዙፍና ኃያል የሆኑ ልጆች ተወለዱ። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን የሰውና የመላእክት ዲቃላዎች ኔፊሊም ብሎ የሚጠራቸው ሲሆን ትርጉሙም “የሚያፈርጡ” ማለት ነው። ጉልበተኛ የሆኑት እነዚህ አረመኔ ኔፊሊሞች በዓለም ላይ ያለው ጭካኔና ክፋት ይበልጥ እንዲባባስ አድርገዋል። በፈጣሪ ዓይን ሲታይ “የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑ” ምንም አያስደንቅም። በመሆኑም ይሖዋ ያንን ክፉ ኅብረተሰብ በ120 ዓመት ውስጥ ጠራርጎ ለማጥፋት ወሰነ።—ዘፍጥረት 6:3-5ን አንብብ።
7. ኖኅና ባለቤቱ ልጆቻቸውን በወቅቱ ከነበረው መጥፎ ተጽዕኖ በመጠበቅ ረገድ ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ነበረባቸው?
7 እንዲህ ባለው ዓለም ውስጥ ልጆችን ማሳደግ ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል * ኖኅና ባለቤቱ ልጆቻቸውን በዙሪያቸው ያለው ዓለም ከሚያሳድረው መጥፎ ተጽዕኖ መጠበቅ ነበረባቸው። ወንዶች ልጆች “በጀግንነታቸው ከፍ ያለ ዝና ያተረፉ” ሰዎችን የማድነቅ ዝንባሌ አላቸው፤ ኔፊሊሞች ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ነበሩ። ኖኅና ባለቤቱ ልጆቻቸው እነዚያ ግዙፍ ሰዎች ስለሚፈጽሙት ጀብዱ ምንም እንዳይሰሙ መከልከል አይችሉም፤ ይሁንና ማንኛውንም ዓይነት ክፋት ስለሚጠላው ስለ ይሖዋ አምላክ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ማስተማር ይችላሉ። በዓለም ላይ የሚታየው ዓመፅና ግፍ ምን ያህል ይሖዋን እንደሚያሳዝነው ልጆቻቸው እንዲያስተውሉ መርዳት ይጠበቅባቸው ነበር።—ዘፍ. 6:6
አስብ! ያም ሆኖ ኖኅ በዚህ ረገድ ተሳክቶለታል። ኖኅ ጥሩ ሚስት ነበረችው፤ እሷም ኖኅ 500 ዓመት ሲሆነው ሴም፣ ካም እና ያፌት የተባሉ ሦስት ወንዶች ልጆችን ወለደችለት።8. በዛሬው ጊዜ የሚገኙ አስተዋይ የሆኑ ወላጆች የኖኅንና የባለቤቱን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?
8 በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆች የኖኅንና የባለቤቱን ስሜት በሚገባ እንደሚረዱላቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ዛሬም ዓለማችን በዓመፅና በግፍ ተሞልቷል። ብዙውን ጊዜ በከተሞች ውስጥ ሥርዓት አልበኛ የሆኑ ወጣቶችን ማየት የተለመደ ነው። ለልጆች ተብለው የሚዘጋጁ መዝናኛዎች እንኳ በዓመፅ ድርጊቶች የተሞሉ ሊሆኑ ይችላሉ። አስተዋይ የሆኑ ወላጆች አንድ ቀን ዓመፅን በሙሉ ስለሚያስወግደውና የሰላም አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋ ልጆቻቸውን በማስተማር እንዲህ ዓይነቱን ተጽዕኖ ለመከላከል የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። (መዝ. 11:5፤ 37:10, 11) ደግሞም በዚህ ረገድ ሊሳካላቸው ይችላል! ኖኅና ሚስቱም ተሳክቶላቸዋል። ልጆቻቸው አድገው ጥሩ ሰዎች የሆኑ ሲሆን ልክ እንደነሱ በሕይወታቸው ውስጥ እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን የሚያስቀድሙ ሚስቶችን አግብተዋል።
“መርከብ ሥራ”
9, 10. (ሀ) ይሖዋ ለኖኅ ሕይወቱን የሚቀይር ምን ትእዛዝ ሰጠው? (ለ) ይሖዋ የመርከቡን ንድፍና ዓላማ በተመለከተ ለኖኅ ምን ነገር ገለጸለት?
9 አንድ ቀን የኖኅን ሕይወት እስከ ወዲያኛው የሚቀይር ሁኔታ ተፈጠረ። ይሖዋ ይህን ውድ አገልጋዩን ያነጋገረው ሲሆን በዘመኑ የነበረውን ዓለም ሊያጠፋው እንዳሰበም ገለጸለት። አምላክም ኖኅን “በጎፈር ዕንጨት መርከብ ሥራ” በማለት አዘዘው።—ዘፍ. 6:14
10 ይህ መርከብ አንዳንዶች እንደሚያስቡት እንደማንኛውም ዓይነት መርከብ አልነበረም። ከፊቱም ሆነ ከኋላው ሲታይ የመርከብ ቅርጽ የለውም፤ አቅጣጫ ማስተካከያ መሪም ቢሆን አልነበረውም። በአጭር አነጋገር ይህ መርከብ አንድ ትልቅ ሣጥን ይመስል ነበር። ይሖዋ ለኖኅ የመርከቡን ትክክለኛ መጠን የነገረው ሲሆን ንድፉን በተመለከተም አንዳንድ ዝርዝር ሐሳቦችን ገልጾለታል፤ በተጨማሪም መርከቡን ከውስጥና ከውጭ በቅጥራን እንዲለቀልቀው መመሪያ ሰጥቶታል። ይሖዋ፣ መርከብ እንዲሠራ ያዘዘው ለምን እንደሆነ ለኖኅ ሲነግረው “እነሆ፤ በምድር ላይ የጥፋት ውሃ አወርዳለሁ፤ በምድር ላይ ያለ ሁሉ ይጠፋል” አለው። በሌላ በኩል ግን ይሖዋ “አንተና ወንዶች ልጆችህ፣ ሚስትህና ዘፍ. 6:17-20
የልጆችህ ሚስቶች ከአንተ ጋር ወደ መርከቧ ትገባላችሁ” በማለት ከኖኅ ጋር ውል ተዋዋለ። በተጨማሪም ኖኅ ከሁሉም ዓይነት የእንስሳት ዝርያ የተወሰኑ እንስሳትን ወደ መርከቡ ማስገባት ነበረበት። ከመጪው የጥፋት ውኃ በሕይወት መትረፍ የሚችሉት ወደ መርከቡ የሚገቡ ብቻ ናቸው!—11, 12. ኖኅ ከፊቱ ምን በጣም ከባድ ሥራ ይጠብቀው ነበር? እሱስ ለዚህ ተፈታታኝ ተልእኮ ምን ምላሽ ሰጠ?
11 ኖኅ ከፊቱ በጣም ከባድ ሥራ ይጠብቀዋል። የሚሠራው መርከብ ርዝመቱ 133 ሜትር፣ ወርዱ 22 ሜትር እንዲሁም ከፍታው 13 ሜትር ስለሆነ በጣም ግዙፍ ነበር። መርከቡ በዘመናችን ካሉ በእንጨት የተሠሩ ግዙፍ የባሕር መርከቦች እንኳ በጣም ይበልጣል። ታዲያ ኖኅ ከሥራው ለመሸሽ ሞክሮ ወይም ሥራው አስቸጋሪ እንደሆነ በመግለጽ አጉረምርሞ ይሆን? አሊያም ደግሞ ሥራውን ለማቅለል ሲል የተሰጠውን ዝርዝር መመሪያ ለመቀየር ሞክሮ ይሆን? በፍጹም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “ኖኅም ሁሉን እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ” ይላል።—ዘፍ. 6:22
12 የመርከቡ ሥራ በርካታ አሥርተ ዓመታት ምናልባትም ከ40 እስከ 50 ዓመት የሚፈጅ ነበር። ሥራው ዛፍ መቁረጥን እንዲሁም ግንዱን ማጓጓዝን፣ መሰንጠቅን፣ መጥረብንና ማገጣጠምን ይጠይቃል። መርከቡ ባለ ሁለት ፎቅ ወይም ደርብ ሲሆን በርካታ ክፍሎች እንዲሁም በጎን በኩል በር ያስፈልገው ነበር። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው መርከቡ ከጣሪያው ትንሽ ዝቅ ብሎ መስኮቶች ያሉት ሲሆን ውኃ በቀላሉ እንዲወርድ ለማስቻል ጣሪያው አሞራ ክንፍ ተደርጎ የተሠራ ነው።—ዘፍ. 6:14-16
13. ኖኅ መርከብ ከመሥራት ይበልጥ ተፈታታኝ ሊሆን የሚችል ምን ሌላ ተልእኮ ተሰጥቶት ነበር? በወቅቱ የነበረውስ ኅብረተሰብ ምን ምላሽ ሰጠ?
13 ዓመታት እያለፉ ሲሄዱና መርከቡም መልክ እየያዘ ሲመጣ ኖኅ የቤተሰቡን ድጋፍ በማግኘቱ በጣም ተደስቶ መሆን አለበት! የተሰጠው ተልእኮ መርከብ ከመሥራት ይበልጥ ተፈታታኝ ሊሆን የሚችል ሌላም ነገር ማከናወንን የሚጠይቅ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ኖኅ “የጽድቅ ሰባኪ” እንደነበር ይናገራል። (2 ጴጥሮስ 2:5ን አንብብ።) በመሆኑም ኖኅ ክፉ የሆነውንና ፈሪሃ አምላክ የሌለውን ኅብረተሰብ ጥፋት እንደተደቀነበት በድፍረት በማስጠንቀቅ ረገድ ግንባር ቀደም ሆኗል። ታዲያ በወቅቱ የነበረው ኅብረተሰብ ምን ምላሽ ሰጠ? ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ያንን ዘመን አስታውሶ ሲናገር ሰዎቹ “ምንም አላስተዋሉም” ብሏል። እነዚህ ሰዎች በዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴዎች ማለትም በመብላት፣ በመጠጣትና በማግባት ተጠምደው ስለነበር ኖኅ ለሰጠው ማስጠንቀቂያ ጆሮ ዳባ ልበስ እንዳሉ ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴ. 24:37-39) ብዙ ሰዎች ኖኅንና ቤተሰቡን መሳለቂያ እንዳደረጓቸው ምንም ጥርጥር የለውም፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ዝተውበትና ከባድ ተቃውሞ አድርሰውበት ይሆናል። ሌላው ቀርቶ የግንባታውን ሥራ ለማስተጓጎል ሞክረው ሊሆን ይችላል።
14. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ቤተሰቦች ከኖኅና ከቤተሰቡ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?
14 ሆኖም ኖኅና ቤተሰቡ ፈጽሞ ተስፋ አልቆረጡም። ምንም እንኳ በዙሪያቸው ያለው ዓለም በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ የሰጡትን ሥራ ከንቱ ድካም፣ ትርጉም የለሽና ሞኝነት እንደሆነ አድርጎ ቢቆጥረውም እነሱ ግን ሥራውን በታማኝነት ማከናወናቸውን ቀጥለዋል። በመሆኑም በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ቤተሰቦች ኖኅና ቤተሰቡ ካሳዩት እምነት ብዙ የሚማሩት ነገር አለ። ደግሞም የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ውስጥ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (2 ጢሞ. 3:1) ኢየሱስ ዘመናችን ኖኅ መርከብ ከሠራበት ዘመን ጋር በጣም እንደሚመሳሰል ተናግሯል። ክርስቲያኖች ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን መልእክት ሲሰብኩ ሰዎች ለመልእክቱ ግዴለሽ ቢሆኑ ወይም ቢያፌዙ አልፎ ተርፎም በእነሱ ላይ ስደት ቢያስነሱ ኖኅን ማስታወሳቸው ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቶቹን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመጋፈጥ እነሱ የመጀመሪያዎቹ አይደሉም።
“ወደ መርከቧ ግባ”
15. ኖኅ 600 ዓመት ሊሞላው ሲል ምን ሐዘን ደረሰበት?
15 አሁን ብዙ አሥርተ ዓመታት አልፈዋል፤ የመርከቡ ሥራም ወደ መጠናቀቁ ተቃርቧል። ኖኅ 600 ዓመት ሊሞላው ሲል ሐዘን ደረሰበት። አባቱ ላሜሕ ሞተ። * ከአምስት ዓመት በኋላ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ከተመዘገቡት ሰዎች ሁሉ ረጅም ዕድሜ የኖረው የላሜሕ አባት፣ የኖኅ አያት ማቱሳላ በ969 ዓመቱ ሞተ። (ዘፍ. 5:27) ማቱሳላም ሆነ ላሜሕ የመጀመሪያው ሰው አዳም በሕይወት ይኖር በነበረበት ዘመን ውስጥ ኖረዋል።
16, 17. (ሀ) ኖኅ በ600 ዓመቱ ምን መመሪያ ተቀበለ? (ለ) ኖኅና ቤተሰቡ የተመለከቱትን ከአእምሮ ሊጠፋ የማይችል ትዕይንት ግለጽ።
16 ኖኅ በ600 ዓመቱ “ቤተ ሰብህን በሙሉ ይዘህ ወደ መርከቧ ግባ” የሚል መመሪያ ከይሖዋ አምላክ ተቀበለ። በተጨማሪም አምላክ ከሁሉም ዓይነት የእንስሳት ዝርያ ይኸውም ለመሥዋዕት ከሚሆኑት ንጹሕ እንስሳት ሰባት ሰባት፣ ከሌሎቹ ደግሞ ሁለት ሁለት እንስሳት ወደ መርከቡ እንዲያስገባ ኖኅን አዘዘው።—ዘፍ. 7:1-3
17 በወቅቱ የነበረው ትዕይንት ፈጽሞ ከአእምሮ ሊጠፋ የማይችል እንደነበር ምንም ዘፍ. 7:9
ጥርጥር የለውም። በሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳት ከየአቅጣጫው እየጎረፉ ነው፤ ከእነዚህ መካከል በእግራቸው የሚሄዱ፣ የሚበርሩ፣ በደረታቸው የሚሳቡ፣ ድክ ድክ የሚሉና እያዘገሙ የሚጓዙ የተለያየ መጠን፣ ቅርጽና ባሕርይ ያላቸው እንስሳት ይገኙበታል። ኖኅ፣ የዱር እንስሳቱን እንደ ልብ መንቀሳቀስ ወደማይችሉበት መርከብ እያስገደደ ወይም እያባበለ ለማስገባት ሲታገል በዓይነ ሕሊናችን ይታየን ይሆናል። ኖኅ ግን እንደዚያ ማድረግ አላስፈለገውም። ምክንያቱም ዘገባው እንስሳቱ “ወደ ኖኅ መጡ፤ . . . ወደ መርከቧ ገቡ” ይላል።—18, 19. (ሀ) ተቺዎች ስለ ኖኅ በሚናገረው ዘገባ ውስጥ የተገለጹትን ክንውኖች አስመልክተው ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መልስ መስጠት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ የፈጠራቸውን እንስሳት ለማዳን የተጠቀመበት ዘዴ ጥበበኛ መሆኑን እንድናስተውል የሚረዳን እንዴት ነው?
18 አንዳንድ ተቺዎች ‘ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ደግሞስ እነዚያ ሁሉ እንስሳት በዚያ ጠባብ ቦታ ውስጥ እንዴት በሰላም አብረው መቆየት ይችላሉ?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። እስቲ አስበው፣ የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ የፈጠራቸውን እንስሳት መቆጣጠር፣ አስፈላጊም ከሆነ ለማዳና ገራም እንዲሆኑ ማድረግ ያቅተዋል? እንስሳትን የፈጠራቸው እሱ ራሱ መሆኑን አትዘንጋ። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ቀይ ባሕርን የከፈለ ሲሆን ፀሐይ ባለችበት እንድትቆም አድርጓል። ታዲያ በኖኅ ታሪክ ውስጥ የተገለጸውን እያንዳንዱን ክንውን መፈጸም ይሳነዋል? በፍጹም ይህን ማድረግ ሊሳነው አይችልም፤ ደግሞም አድርጎታል!
19 አምላክ የፈጠራቸውን እንስሳት በሌላ መንገድ ማዳን ይችል እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ አምላክ ሰዎችን በፈጠረበት ወቅት በምድር ላይ ያሉትን ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ እንዲንከባከቡ የሰጣቸውን ኃላፊነት እንድናስታውስ የሚያደርገንን ዘዴ መጠቀም መርጧል። (ዘፍ. 1:28) በዚህም ምክንያት በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ወላጆች ይሖዋ የፈጠራቸውን እንስሳትም ሆነ ሰዎች ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ለልጆቻቸው ለማስተማር የኖኅን ታሪክ ይጠቀማሉ።
20. ኖኅና ቤተሰቡ የጥፋት ውኃው ከመምጣቱ በፊት በነበረው የመጨረሻ ሳምንት በምን ሥራ ተጠምደው ሊሆን ይችላል?
20 ይሖዋ የጥፋት ውኃው በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንደሚመጣ ለኖኅ ነገረው። መቼም ያ ሳምንት ለኖኅና ለቤተሰቡ ውጥረት የበዛበት እንደሚሆን ግልጽ ነው። እንስሳቱንም ሆነ ለእንስሳቱና ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ቀለብ ወደ መርከቡ አስገብቶ ቦታ ቦታ ማስያዝ እንዲሁም የቤተሰቡን ንብረት ተሸክሞ ወደ መርከቡ ማስገባት ምን ያህል አድካሚ ሊሆን እንደሚችል ገምት። በተለይ የኖኅ፣ የሴም፣ የካም እና የያፌት ሚስቶች መርከቡን ቤት ለማስመሰል ደፋ ቀና ሲሉ ቆይተው መሆን አለበት።
21, 22. (ሀ) በኖኅ ዘመን የነበሩት ሰዎች ግዴለሽ መሆናቸው ሊያስገርመን የማይገባው ለምንድን ነው? (ለ) በኖኅና በቤተሰቡ ላይ ሲያፌዙ የነበሩት ሰዎች ማፌዛቸውን ያቆሙት መቼ ነው?
21 ይህ ሁሉ ሲሆን በዙሪያቸው ያሉት ሰዎች ምን ያደርጉ ነበር? ይሖዋ ኖኅንም ሆነ ሥራውን እየባረከ እንዳለ ቢመለከቱም “ምንም አላስተዋሉም።” እንስሳቱ ወደ መርከቡ እየጎረፉ ሲገቡ ቆመው ከማየት ውጭ ምንም ያደረጉት ነገር የለም። ይሁን እንጂ ግዴለሽ መሆናቸው ሊያስገርመን አይገባም። በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎችም የምንኖረው በዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ መሆኑን የሚያሳዩትን በርካታ ማስረጃዎች አያስተውሉም። በተጨማሪም ሐዋርያው ጴጥሮስ በተናገረው ትንቢት መሠረት የአምላክን ማስጠንቀቂያ ሰምተው እርምጃ በሚወስዱ ግለሰቦች ላይ የሚያፌዙ ፌዘኞች አሉ። (2 ጴጥሮስ 3:3-6ን አንብብ።) በተመሳሳይም ሰዎች በኖኅና በቤተሰቡ ላይ አፊዘውባቸው እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።
22 ታዲያ ፌዙ የቆመው መቼ ነው? ዘገባው ኖኅ ቤተሰቡንና እንስሳቱን ወደ መርከቡ ካስገባ በኋላ ይሖዋ በሩን ‘ከውጭ እንደዘጋበት’ ይነግረናል። በአቅራቢያው ያለ ማንኛውም ፌዘኛ አምላክ የወሰደውን ይህን እርምጃ ሲመለከት ማፌዙን እንደሚያቆም ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ እንኳ ባይሆን ዝናቡ መዝነብ መጀመሩ ጸጥ እንደሚያሰኘው ግልጽ ነው! አዎ፣ ዝናቡ ያለማቋረጥ መዝነብ ጀመረ፤ በዚህም የተነሳ ልክ ይሖዋ እንደተናገረው መላው ዓለም በውኃ ተጥለቀለቀ።—ዘፍ. 7:16-21
23. (ሀ) ይሖዋ በኖኅ ዘመን የነበሩት ክፉ ሰዎች ሞት እንዳላስደሰተው እንዴት ማወቅ እንችላለን? (ለ) ዛሬም እምነት በማሳየት ረገድ የኖኅን ምሳሌ መከተላችን የጥበብ አካሄድ የሆነው ለምንድን ነው?
23 የእነዚያ ክፉ ሰዎች ሞት ይሖዋን ያስደስተዋል? በፍጹም! (ሕዝ. 33:11) እንዲያውም ይሖዋ አካሄዳቸውን አስተካክለው ትክክለኛውን ነገር ማድረግ የሚችሉበትን አጋጣሚ ሁሉ ሰጥቷቸው ነበር። ታዲያ ይህን ማድረግ ይችሉ ነበር? ይህን ማድረግ ይችሉ እንደነበር የኖኅ ሕይወት ያሳያል። ኖኅ ከይሖዋ ጋር በመሄድ ይኸውም በሁሉም ነገር አምላኩን በመታዘዝ ከጥፋት መትረፍ እንደሚቻል አሳይቷል። በዚህ መንገድ ኖኅ በእምነቱ አማካኝነት በዘመኑ የነበረውን ዓለም ኮንኗል፤ በዚያን ጊዜ የነበረው ትውልድ ምን ያህል ክፉ እንደሆነ አጋልጧል። ኖኅ በእምነቱ እሱንም ሆነ ቤተሰቡን አድኗል። አንተም እምነት በማሳየት ረገድ የኖኅን ምሳሌ የምትከተል ከሆነ ራስህንም ሆነ የምትወዳቸውን ሰዎች ታድናለህ። ልክ እንደ ኖኅ ይሖዋ አምላክን ወዳጅህ በማድረግ ከእሱ ጋር መሄድ ትችላለህ። ይህ ወዳጅነት ደግሞ ዘላቂ ሊሆን ይችላል!
^ አን.3 ዘፍጥረት 6:9 (NW)፦ “የኖኅ ታሪክ ይህ ነው። ኖኅ ጻድቅ ሰው ነበር። በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች መካከል እሱ እንከን የሌለበት ሰው ነበር። ኖኅ ከእውነተኛው አምላክ ጋር ይሄድ ነበር።”
^ አን.7 በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች ከእኛ የበለጠ ረጅም ዕድሜ ይኖሩ ነበር። ይህ ሊሆን የቻለው በዚያ ዘመን የነበረው ትውልድ በአንድ ወቅት ጠንካራና ፍጹም ለነበሩት ለአዳምና ለሔዋን ቅርብ በመሆኑ እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።
^ አን.15 ላሜሕ ለልጁ ኖኅ የሚል ስም ያወጣለት ሲሆን ትርጉሙ “እረፍት” ወይም “መጽናኛ” ማለት ሊሆን ይችላል፤ በተጨማሪም ላሜሕ፣ ኖኅ በተረገመችው ምድር ላይ የሰውን ዘር ከድካሙ በማሳረፍ ከስሙ ትርጉም ጋር የሚስማማ ተግባር እንደሚፈጽም ትንቢት ተናግሯል። (ዘፍ. 5:28, 29) ሆኖም ላሜሕ ቀደም ብሎ በመሞቱ ይህ ትንቢት ሲፈጸም ማየት አልቻለም። የኖኅ እናት እንዲሁም ወንድሞቹና እህቶቹ በጥፋት ውኃው ጠፍተው ሊሆን ይችላል።