በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አሥራ ስድስት

ለሕዝቧ ስትል ሕይወቷን ለአደጋ ያጋለጠች ጠቢብና ደፋር ሴት

ለሕዝቧ ስትል ሕይወቷን ለአደጋ ያጋለጠች ጠቢብና ደፋር ሴት

1-3. (ሀ) አስቴር ወደ ባሏ ዙፋን በቀረበችበት ጊዜ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? (ለ) ንጉሡ፣ አስቴር ወደ እሱ ስትመጣ ምን ምላሽ ሰጣት?

አስቴር ልቧ በኃይል እየመታ በቀስታ ወደ ዙፋኑ ቀረበች። በሱሳ በሚገኘው የፋርስ ቤተ መንግሥት ታላቅ ንጉሣዊ አዳራሽ ውስጥ የሰፈነውን ጸጥታ ለማሰብ ሞክር፤ አዳራሹ ረጭ ከማለቱ የተነሳ አስቴር የራሷንም ኮቴ ሆነ የለበሰችው የክብር ልብስ ሲንሿሿ መስማት ትችላለች። በዚህ ወቅት አስቴር፣ ትልቅ ስለሆነው የቤተ መንግሥቱ አደባባይ፣ ግርማ ሞገስ ስለተላበሱት ዓምዶች እንዲሁም ከሩቅ አገር ከሊባኖስ በመጣ ዝግባ ስለተሠራው ኮርኒስ ልታስብ አትችልም። ትኩረቷ ሁሉ ያረፈው በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ግለሰብ ላይ ነው፤ ምክንያቱም ሕይወቷ በእሱ እጅ ነው።

2 ንጉሡ፣ አስቴር ወደ እሱ እየቀረበች ስትመጣ ትኩር ብሎ ተመለከታት፤ ከዚያም የወርቅ ዘንጉን ዘረጋላት። ይህ ድርጊት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ባይመስልም የአስቴርን ሕይወት አትርፎላታል፤ ምክንያቱም ንጉሡ ዘንጉን መዘርጋቱ፣ አስቴር ንጉሡ ሳይጠራት ወደ እሱ በመምጣት ለፈጸመችው ጥፋት ይቅርታ እንዳደረገላት የሚያሳይ ነው። አስቴርም ዙፋኑ አጠገብ ስትደርስ አመስጋኝነቷን ለማሳየት እጇን ዘርግታ የዘንጉን ጫፍ ነካች።—አስ. 5:1, 2

አስቴር ንጉሡ ላሳያት ምሕረት አመስጋኝ መሆኗን በትሕትና ገልጻለች

3 ንጉሥ ጠረክሲስ እጅግ ባለጸጋ እንደሆነና ታላቅ ኃይል እንዳለው በግልጽ ማየት ይቻላል። በዚያ ዘመን የፋርስ ነገሥታት የሚለብሱት ንጉሣዊ ልብስ በአሁኑ ጊዜ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንደሚያወጣ ይታመናል። ያም ሆኖ ንጉሡ ለአስቴር ለየት ያለ ፍቅር ነበረው፤ እሷም ብትሆን ይህን ከዓይኑ ላይ ማንበብ ችላለች። ንጉሡ እንዲህ አላት፦ “ንግሥት አስቴር ሆይ፤ ለምን መጣሽ? ከእኔ የምትፈልጊውስ ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ቢሆን ይሰጥሻል።”—አስ. 5:3

4. አስቴር ከፊቷ ምን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይጠብቋታል?

4 አስቴር ሕዝቧን ከምድር ገጽ ለመደምሰስ ከተጠነሰሰው ሴራ ለመታደግ ስትል ወደ ንጉሡ መምጣቷ በራሱ አስደናቂ እምነትና ድፍረት እንዳላት የሚያሳይ ነው። እስካሁን ያሰበችው ተሳክቶላታል፤ ሆኖም ይበልጥ አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎች ከፊቷ ይጠብቋታል። ኩሩ የሆነውን ይህን ንጉሥ፣ በጣም የሚያምነው አማካሪው እሱን በማታለል በሕዝቧ ላይ ሞት እንዲፈርድ ያደረገ ክፉ ሰው መሆኑን ማሳመን ይኖርባታል። ታዲያ አስቴር፣ ንጉሡን እንዴት አድርጋ ታሳምነው ይሆን? እኛስ እሷ ካሳየችው እምነት ምን ልንማር እንችላለን?

‘የምትናገርበትን ጊዜ’ በጥበብ መርጣለች

5, 6. (ሀ) አስቴር በ⁠መክብብ 3:1, 7 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ያደረገችው እንዴት ነው? (ለ) አስቴር ባሏን ያነጋገረችበት መንገድ ጥበብ የተንጸባረቀበት ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

5 አስቴር፣ በንጉሡ ሹማምንት ፊት ጉዳይዋን ግልጥልጥ አድርጋ ለንጉሡ ብትነግረው ይሻል ይሆን? እንዲህ ብታደርግ ኖሮ ንጉሡ ለውርደት ሊዳረግ እንዲሁም አማካሪው ሐማ የሰነዘረችበትን ክስ የሚያስተባብልበት ጊዜ ሊያገኝ ይችል ነበር። ታዲያ አስቴር ምን አደረገች? ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ . . . ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው” በማለት በመንፈስ መሪነት ጽፎ ነበር። (መክ. 3:1, 7) የአስቴር አሳዳጊ አባት የሆነው ታማኙ መርዶክዮስ ይህቺን ወጣት ተንከባክቦ ባሳደጋት ወቅት እንዲህ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት አስተምሯት እንደሚሆን ልንገምት እንችላለን። አስቴር ‘የምትናገርበትን ጊዜ’ በጥንቃቄ የመምረጥን አስፈላጊነት እንደተገነዘበች ጥርጥር የለውም።

6 አስቴር “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ቢሆን፣ ባዘጋጀሁለት ግብዣ ላይ ንጉሡ ዛሬ ከሐማ ጋር ይገኝልኝ” አለች። (አስ. 5:4) ንጉሡ ግብዣውን የተቀበለ ሲሆን ሐማንም አስጠራው። የአስቴር አነጋገር ጥበብ የተንጸባረቀበት እንደነበር አስተዋልክ? የባሏን ክብር የሚነካ ነገር ሳታደርግ ያሳሰባትን ነገር ለእሱ ለመንገር የሚያስችል ሁኔታ አመቻቸች።—ምሳሌ 10:19ን አንብብ።

7, 8. አስቴር በመጀመሪያ ያዘጋጀችው ግብዣ ምን ይመስል ነበር? ሆኖም በዚህ ወቅት ጉዳይዋን ለንጉሡ መናገር ያልፈለገችው ለምንድን ነው?

7 አስቴር ግብዣውን በጥንቃቄ እንዳዘጋጀችና ሁሉም ነገር ልክ ባሏ በሚፈልገው መንገድ መሠራቱን እንደተከታተለች ጥርጥር የለውም። ግብዣው ደስ የሚያሰኝ እንዲሆን ምርጥ የወይን ጠጅ ቀርቦ ነበር። (መዝ. 104:15) ጠረክሲስ በግብዣው ስለተደሰተ አስቴር የምትፈልገውን ነገር እንድትነግረው በድጋሚ ጠየቃት። አስቴር ጉዳዩን አሁን ብትነግረው ይሻል ይሆን?

8 አስቴር አሁን መናገር እንዳለባት አልተሰማትም። ከዚህ ይልቅ ንጉሡንና ሐማን በቀጣዩ ቀን በምታዘጋጀው ሌላ ግብዣ ላይ እንዲገኙ ጠራቻቸው። (አስ. 5:7, 8) አስቴር በዚህ ወቅት መናገር ያልፈለገችው ለምንድን ነው? ንጉሡ ባወጣው አዋጅ የተነሳ የአስቴር ሕዝብ በሙሉ ከምድር ገጽ የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠበት አስታውስ። ከጉዳዩ ክብደት አንጻር አስቴር የምትናገርበትን ጊዜ በጥንቃቄ መምረጥ ነበረባት። በመሆኑም ባሏን ምን ያህል እንደምታከብረው የምታሳይበት ሌላ አጋጣሚ ለመፍጠር ስትል የምትናገርበትን ጊዜ አዘገየችው።

9. ትዕግሥት ምን ያህል ተፈላጊ ባሕርይ ነው? አስቴር በዚህ ረገድ የተወችውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

9 ትዕግሥት ብዙ ሰዎች የሌላቸው ውድ ባሕርይ ነው። አስቴር ጉዳዩ ያስጨነቃትና በልቧ ውስጥ ያለውን ለመናገር ጓጉታ የነበረ ቢሆንም የምትናገርበትን ትክክለኛ ጊዜ በትዕግሥት ጠብቃለች። እኛም አስቴር ከተወችው ምሳሌ ብዙ መማር እንችላለን፤ ሁላችንም ሊስተካከሉ የሚገቡ ስህተቶችን ማየታችን አይቀርም። በሥልጣን ላይ ያለ አንድ ሰው የገጠመንን ችግር እንዲፈታልን ለማሳመን ከፈለግን የአስቴርን ምሳሌ በመከተል ትዕግሥተኞች መሆን ሊያስፈልገን ይችላል። ምሳሌ 25:15 “በትዕግሥት ገዥን ማግባባት ይቻላል፤ ለስላሳ አንደበትም ዐጥንት ይሰብራል” ይላል። አስቴር እንዳደረገችው በትዕግሥት ትክክለኛውን ጊዜ ጠብቀን በለሰለሰ አንደበት የምንናገር ከሆነ እንደ አጥንት ጠንካራ የሆነ ተቃውሞን እንኳ መስበር እንችላለን። ታዲያ አስቴር ትዕግሥተኛና ጠቢብ መሆኗ የአምላኳን የይሖዋን በረከት አስገኝቶላታል?

ትዕግሥት ለፍትሕ መንገድ ይጠርጋል

10, 11. ሐማ ከመጀመሪያው ግብዣ ከወጣ በኋላ ደስታው እንዲጠፋ ያደረገው ምን ነበር? ሚስቱና ወዳጆቹስ ምን እንዲያደርግ መከሩት?

10 አስቴር ያሳየችው ትዕግሥት እርስ በርስ ተያያዥነት ያላቸው አስገራሚ የሆኑ ነገሮች እንዲከናወኑ መንገድ ጠርጓል። ሐማ የንጉሡንና የንግሥቲቱን ሞገስ እንዳገኘ ስለተሰማው ከመጀመሪያው ግብዣ በኋላ ወደ ቤቱ ሲመለስ “ደስ ብሎትና መንፈሱ ረክቶ” ነበር። ይሁንና ሐማ በቤተ መንግሥቱ በር በኩል ሲያልፍ ዓይኑ መርዶክዮስ ላይ አረፈ፤ ይህ አይሁዳዊ አሁንም ቢሆን ለእሱ ለመስገድ ፈቃደኛ አልሆነም። ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው መርዶክዮስ ለሐማ የማይሰግደው ስለናቀው ሳይሆን ይህን ለማድረግ ሕሊናው ስላልፈቀደለትና ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለውን ዝምድና እንደሚነካበት ስለተሰማው ነው። ሆኖም ሐማ፣ መርዶክዮስ እንዳልሰገደለት ሲመለከት “ቁጣው . . . ነደደ።”—አስ. 5:9

11 ሐማ ለሚስቱና ለወዳጆቹ መርዶክዮስ ሊሰግድለት ፈቃደኛ አለመሆኑን ሲነግራቸው ቁመቱ ከ22 ሜትር በላይ የሚሆን ትልቅ ግንድ እንዲያስተክልና መርዶክዮስን ለመስቀል ከንጉሡ ፈቃድ እንዲጠይቅ መከሩት። ሐማ በሰጡት ሐሳብ ስለተደሰተ ወዲያውኑ ያሉትን ለማድረግ ቆርጦ ተነሳ።—አስ. 5:12-14

12. ንጉሡ የዘመኑ የታሪክ መዛግብት ከፍ ባለ ድምፅ እንዲነበቡለት የጠየቀው ለምንድን ነው? በዚህ ጊዜስ ምን ተረዳ?

12 ይህ በእንዲህ እንዳለ “በዚያች ሌሊት ንጉሡ እንቅልፍ መተኛት አልቻለም።” በመሆኑም የዘመኑ የታሪክ መዛግብት ከፍ ባለ ድምፅ እንዲነበቡለት አዘዘ። መዛግብቱ ሲነበቡ በጠረክሲስ ላይ ተጠንስሶ ስለነበረው የግድያ ሴራ የሚናገር ዘገባ ሰፍሮ ተገኘ። ንጉሡም ጉዳዩን አስታወሰ፤ ሊገድሉት ያሴሩት ሰዎች ተይዘው በሞት ተቀጥተው ነበር። ይሁንና ሴራውን ያጋለጠው መርዶክዮስስ ምን ተደረገለት? ንጉሡ፣ መርዶክዮስ ምን ሽልማት እንደተሰጠው ጠየቀ። በዚህ ጊዜ ምንም እንዳልተደረገለት ተነገረው።—አስቴር 6:1-3ን አንብብ።

13, 14. (ሀ) ሐማ ነገሮች እየተበላሹበት የሄዱት እንዴት ነው? (ለ) ለሐማ ሚስቱና ወዳጆቹ ምን ነገሩት?

13 ንጉሡም በሁኔታው በማዘን የተፈጠረውን ስህተት ለማስተካከል ሊረዳው የሚችል የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን በአቅራቢያው ይገኝ እንደሆነ ጠየቀ። የሚገርመው ነገር፣ በንጉሡ ቤተ መንግሥት አደባባይ የተገኘው ሐማ ነበር፤ ሐማ እንዲህ ማልዶ የመጣው መርዶክዮስን ለማስገደል የሚያስችለውን ፈቃድ ከንጉሡ ለማግኘት ጓጉቶ ሳይሆን አይቀርም። ይሁን እንጂ ሐማ ፈቃድ ከመጠየቁ በፊት ጠረክሲስ፣ ንጉሡ ሊያከብረው ለሚፈልገው ሰው ምን ቢደረግለት እንደሚሻል ጠየቀው። ሐማም ንጉሡ ይህን ሊያደርግለት የሚፈልገው ሰው ከእሱ ሌላ ማንም ሊሆን እንደማይችል አሰበ። በመሆኑም ሐማ፣ ለግለሰቡ ታላቅ ክብር ሊሰጠው እንደሚገባ ተናገረ፤ ንጉሡ ሊያከብረው የሚፈልገው ሰው የንጉሡን ልብሰ መንግሥት እንዲለብስና አንድ ትልቅ ባለሥልጣን በንጉሡ ፈረስ ላይ አስቀምጦት በሱሳ ከተማ እንዲያዘዋውረው እንዲሁም ሁሉ ሰው እየሰማ ጮክ ብሎ እንዲያወድሰው ሐሳብ አቀረበ። ሐማ እንዲህ ያለው ክብር ሊሰጠው የታሰበው ሰው መርዶክዮስ መሆኑን ሲያውቅ ፊቱ ምን ያህል እንደተለዋወጠ መገመት ትችላለህ! ይባስ ብሎ ደግሞ ንጉሡ የመርዶክዮስን ክብር እንዲያውጅ የመደበው ሐማን ነበር!—አስ. 6:4-10

14 ሐማ የተሰጠውን ሥራ ሳይወድ በግዱ ከፈጸመ በኋላ አንጀቱ እርር ብሎ ወደ ቤቱ ተመለሰ። ሚስቱና ወዳጆቹ፣ እንዲህ ያለ ያልተጠበቀ ሁኔታ መከሰቱ መጨረሻው እንደማያምር የሚጠቁም መሆኑን እንዲሁም መርዶክዮስ ከተባለው ከዚህ አይሁዳዊ ጋር በገጠመው ትግል መሸነፉ እንደማይቀር ነገሩት።—አስ. 6:12, 13

15. (ሀ) አስቴር መታገሷ ምን መልካም ውጤት አስገኘ? (ለ) በትዕግሥት ‘የመጠበቅ’ ዝንባሌ ማዳበራችን ጥበብ የሆነው ለምንድን ነው?

15 አስቴር ልመናዋን ለንጉሡ ለማቅረብ አንድ ተጨማሪ ቀን ታግሣ መቆየቷ ሐማ ለራሱ ውድቀት ሁኔታዎችን እንዲያመቻች አጋጣሚ ፈጠረ። ምናልባት በዚያ ሌሊት ንጉሡ እንቅልፍ እንዲያጣ ያደረገው ይሖዋ አምላክ ይሆን? (ምሳሌ 21:1) የአምላክ ቃል በትዕግሥት ‘የመጠበቅ’ ዝንባሌ እንድናዳብር የሚያበረታታን ያለ ምክንያት አይደለም! (ሚክያስ 7:7ን አንብብ።) አምላክን በትዕግሥት የምንጠብቅ ከሆነ እሱ ለችግሮቻችን የሚሰጠው መፍትሔ እኛ ከምንፈጥረው ብልሃት እጅግ የላቀ መሆኑን ማስተዋል እንችላለን።

በድፍረት ተናገረች

16, 17. (ሀ) አስቴር ‘የምትናገርበት ጊዜ’ እንደደረሰ የተሰማት መቼ ነበር? (ለ) አስቴር ከቀድሞዋ የንጉሡ ሚስት ከአስጢን የተለየች የነበረችው እንዴት ነው?

16 አስቴር ከዚህ በላይ የንጉሡን ትዕግሥት መፈታተን አልፈለገችም፤ በመሆኑም በሁለተኛው ግብዣ ላይ ሁሉንም ነገር ልትነግረው ወሰነች። ግን እንዴት አድርጋ ትንገረው? ደግነቱ ንጉሡ ራሱ ምን እንዲደረግላት እንደምትፈልግ በድጋሚ ስለጠየቃት ጉዳይዋን የምትናገርበት አጋጣሚ አገኘች። (አስ. 7:2) በመጨረሻ አስቴር ‘የምትናገርበት ጊዜ’ ደረሰ።

17 አስቴር የሚከተለውን ሐሳብ ከመናገሯ በፊት በልቧ ወደ አምላኳ ጸልያ እንደሚሆን መገመት እንችላለን፦ “ንጉሥ ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼና ግርማዊነትህን ደስ የሚያሰኝ ከሆነ፣ ሕይወቴን ታደጋት፤ ልመናዬ ይህ ነው፤ ሕዝቤን አትርፍ፤ ጥያቄዬም ይኸው ነው።” (አስ. 7:3) አስቴር፣ ንጉሡ ደስ የሚያሰኘውን ውሳኔ ቢያስተላልፍ ውሳኔውን ለማክበር ዝግጁ መሆኗን እንደገለጸች ልብ በል። አስቴር፣ ንጉሡን ሆን ብላ ካዋረደችው ከቀድሞዋ ሚስቱ ከአስጢን ምንኛ የተለየች ነበረች! (አስ. 1:10-12) ከዚህም በላይ አስቴር፣ ንጉሡ በሐማ ላይ እምነት መጣሉ ሞኝነት እንደሆነ በመናገር አልነቀፈችውም። ከዚህ ይልቅ በሕይወቷ ላይ ከተጋረጠው አደጋ እንዲጠብቃት ንጉሡን ለመነችው።

18. አስቴር የገጠማትን ችግር ለንጉሡ የነገረችው እንዴት ነው?

18 ይህ ልመና ንጉሡን እንዳስደነገጠውና እንዳስገረመው ጥርጥር የለውም። ለመሆኑ ማን ነው እንዲህ ደፍሮ ንግሥቲቱን ለመጉዳት የቃጣው? አስቴር በመቀጠል እንዲህ አለች፦ “እኔና ሕዝቤ ለጥፋት፣ ለመገደልና ለመደምሰስ ተሸጠናል። የተሸጥነው ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎች እንድንሆን ብቻ ቢሆን ኖሮ ዝም ባልኩ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ጥፋት በንጉሡም ላይ ጉዳት ስለሚያስከትል በቸልታ መታለፍ የለበትም።” (አስ. 7:4 NW) አስቴር የገጠማትን ችግር በግልጽ እንደተናገረች ልብ በል፤ ሆኖም ችግሩ ለባርነት የመዳረግ ጉዳይ ቢሆን ኖሮ በዝምታ ታልፈው እንደነበር አክላ ገልጻለች። ይሁንና ይህ የዘር ማጥፋት ሴራ በንጉሡ ላይ ከባድ ኪሣራ ስለሚያስከትል በዝምታ ሊታለፍ አይገባም።

19. የማሳመን ችሎታን በተመለከተ ከአስቴር ምን እንማራለን?

19 አስቴር የተወችው ምሳሌ የማሳመን ችሎታን በተመለከተ ብዙ ነገር ያስተምረናል። ለምትወደው ሰው ወይም ለአንድ ባለሥልጣን ስላሳሰበህ ጉዳይ መናገር ቢያስፈልግህ ሐሳብህን በትዕግሥት፣ በአክብሮትና በግልጽነት ለማስረዳት መሞከርህ ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል።—ምሳሌ 16:21, 23

20, 21. (ሀ) አስቴር ሐማን ያጋለጠችው እንዴት ነው? ንጉሡስ ምን ተሰማው? (ለ) ሐማ ያልታወቀበት መሠሪ ጠላት መሆኑ ሲጋለጥ ምን አደረገ?

20 ጠረክሲስ “ለመሆኑ እርሱ ማን ነው? እንዲህ ያለውን ነገር ለማድረግ እስከዚህ የደፈረውስ ሰው የታለ?” ሲል ጠየቀ። አስቴር ጣቷን በሐማ ላይ ቀስራ “ያ ባላጋራና ጠላት ይህ ክፉው ሐማ ነው” ስትል በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። አስቴር የሰነዘረችው ከባድ ክስ ምን ዓይነት ስሜት ፈጥሮ ይሆን? ሐማ በድንጋጤ ክው ብሎ ቀረ። ቁጡ የሆነው ንጉሥ ደግሞ የሚያምነው አማካሪው እንዳታለለውና የሚወዳት ሚስቱ እንድትገደል በሚያዝዝ ሰነድ ላይ እንዲፈርም እንዳደረገው በተገነዘበ ጊዜ ፊቱ በንዴት እንደቀላ መገመት አያዳግትም! ንጉሡ ቁጣው እንዲበርድለት ወደ አትክልቱ ስፍራ ሄደ።—አስ. 7:5-7

አስቴር የሐማን ክፋት በድፍረት አጋልጣለች

21 ሐማ ያልታወቀበት መሠሪ ጠላት መሆኑ ሲጋለጥ በንግሥቲቱ እግር ላይ ተደፋ። ንጉሡ ተመልሶ ሲመጣ ሐማ፣ አስቴርን በድንክ አልጋዋ ላይ ተደፍቶ ሲማጸናት አገኘው፤ በዚህ ጊዜ ንጉሡ ተናድዶ ንግሥቲቱን በገዛ ቤቱ ሊደፍራት እንደሞከረ አድርጎ ወነጀለው። ይህ ክስ ሐማ ሞት እንደሚጠብቀው የሚጠቁም ነበር። ከዚያም ሐማ ፊቱ ተሸፍኖ እንዲወሰድ ተደረገ። በዚህ ጊዜ ከንጉሡ ጃንደረቦች አንዱ፣ ሐማ መርዶክዮስን ሊሰቅልበት አስቦ ያስተከለው ትልቅ ግንድ እንዳለ ለንጉሡ ነገረው። ጠረክሲስም ሐማ ራሱ በዚያ ግንድ ላይ እንዲሰቀል ወዲያውኑ አዘዘ።—አስ. 7:8-10

22. አስቴር የተወችው ምሳሌ ፈጽሞ ተስፋ መቁረጥም ሆነ መጠራጠር አሊያም እምነት ማጣት እንደሌለብን የሚያስተምረን እንዴት ነው?

22 ፍትሕ በጠፋበት በዛሬው ጊዜ ፍትሐዊ እርምጃ ሲወሰድ እናያለን ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። አንተስ እንደዚህ ተሰምቶህ ያውቃል? አስቴር ፈጽሞ ተስፋ አልቆረጠችም፣ አልተጠራጠረችም ወይም እምነት አላጣችም። በተገቢው ጊዜ ትክክል ስለሆነው ነገር በድፍረት የተናገረች ሲሆን ይሖዋ እንደሚረዳት በመተማመን የቀረውን ለእሱ ትታለች። እኛም እንዲሁ እናድርግ! ይሖዋ ዛሬም ቢሆን አልተለወጠም። በመሆኑም በሐማ ላይ እንዳደረገው ሁሉ ክፉና አታላይ የሆኑ ሰዎች በራሳቸው ወጥመድ እንዲወድቁ ማድረግ ይችላል።—መዝሙር 7:11-16ን አንብብ።

ለይሖዋና ለሕዝቡ በመቆርቆር እርምጃ ወስዳለች

23. (ሀ) ንጉሡ ለመርዶክዮስና ለአስቴር ምን አደረገላቸው? (ለ) ያዕቆብ ሊሞት በተቃረበበት ወቅት ስለ ቢንያም የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? ( “አንድ ትንቢት ፍጻሜውን አገኘ” የሚል ርዕስ ያለውን ሣጥን ተመልከት።)

23 በመጨረሻም ንጉሡ፣ መርዶክዮስ ማን እንደሆነ አወቀ፤ ከተጠነሰሰበት የግድያ ሴራ ያዳነው ታማኝ ሰው ብቻ ሳይሆን የአስቴር አሳዳጊ አባትም መሆኑን ተገነዘበ። ጠረክሲስ ሐማ የነበረውን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን ለመርዶክዮስ ሰጠው። ንጉሡ የሐማን ቤትና የነበረውን ከፍተኛ ሀብት ለአስቴር ሰጣት፤ እሷ ደግሞ መርዶክዮስን በሐማ ንብረት ላይ ሾመችው።—አስ. 8:1, 2

24, 25. (ሀ) አስቴር የሐማ ሴራ ከተጋለጠም በኋላ እፎይ ብላ መቀመጥ የማትችለው ለምንድን ነው? (ለ) አስቴር ለሁለተኛ ጊዜ ሕይወቷን ለአደጋ ያጋለጠችው እንዴት ነው?

24 አስቴርና መርዶክዮስ ከሞት ስለተረፉ ንግሥቲቱ እፎይ ማለት ትችል ይሆን? ይህ ሊሆን የሚችለው ራስ ወዳድ ከሆነች ብቻ ነው። ሐማ አይሁዳውያንን በሙሉ ለመፍጀት ያወጣው አዋጅ በዚህ ወቅት በግዛቱ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር እየተዳረሰ ነበር። ሐማ ይህን አረመኔያዊ ጥቃት ለመፈጸም አመቺ የሚሆነውን ጊዜ ለይቶ ለማወቅ ፉር ወይም ዕጣ ጥሎ ነበር፤ ይህ ዕጣ ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም። (አስ. 9:24-26) አይሁዳውያንን ለማጥፋት የታሰበው ቀን ሊደርስ ወራት የሚቀሩት ቢሆንም ጊዜው በፍጥነት ማለፉ አይቀርም። ይህ እልቂት እንዳይደርስ ማድረግ ይቻል ይሆን?

25 አስቴር ለሁለተኛ ጊዜ ሕይወቷን ለአደጋ በማጋለጥ ንጉሡ ሳይጠራት ፊቱ ቀረበች። በዚህ ጊዜ አስቴር ንጉሡ እግር ላይ ወድቃ ስለ ሕዝቧ በማልቀስ የወጣውን አሰቃቂ አዋጅ እንዲሽር ባሏን ለመነችው። ይሁን እንጂ በፋርስ ነገሥታት ስም የተላለፈ ሕግ ሊሻር አይችልም። (ዳን. 6:12, 15) ስለዚህ ንጉሡ አዲስ ሕግ እንዲያጸድቁ ለአስቴርና ለመርዶክዮስ ሥልጣን ሰጣቸው። በመሆኑም አይሁዳውያን ራሳቸውን እንዲከላከሉ መብት የሚሰጣቸው ሁለተኛ አዋጅ ወጣ። ከዚያም ፈረሰኞች በግዛቱ ውስጥ ወዳሉት ስፍራዎች ሁሉ በፍጥነት በመሄድ ለአይሁዳውያን ምሥራቹን አዳረሱ። ብዙዎች የመኖር ተስፋቸው እንደገና ለመለመ። (አስ. 8:3-16) በዚያ ሰፊ ግዛት በሙሉ የሚኖሩ አይሁዳውያን ራሳቸውን ሲያስታጥቁና ለውጊያ ሲዘጋጁ በዓይነ ሕሊናችን መመልከት እንችላለን፤ አዲሱ አዋጅ ባይወጣ ኖሮ ይህ ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነገር ነበር። ይሁንና አሁን የሚነሳው ትልቅ ጥያቄ ‘የሰራዊት አምላክ’ የሆነው ይሖዋ ከሕዝቡ ጎን ይቆም ይሆን? የሚለው ነው።—1 ሳሙ. 17:45

አስቴርና መርዶክዮስ ያወጡትን አዋጅ በፋርስ ግዛት ለሚገኙ አይሁዳውያን ሁሉ አስተላልፈዋል

26, 27. (ሀ) ይሖዋ ሕዝቦቹን በጠላቶቻቸው ላይ ያቀዳጃቸው ድል ምን ያህል ታላቅና ሰፊ ነበር? (ለ) የሐማ ልጆች መገደላቸው የትኛው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ አደረገ?

26 አይሁዳውያንን ለማጥፋት የተመረጠው ቀን ሲደርስ የአምላክ ሕዝቦች ተዘጋጅተው ነበር። ስለ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስለ አይሁዳዊው መርዶክዮስ የሚገልጸው ዜና በሁሉም ቦታ ስለተዳረሰ ብዙ የፋርስ ባለሥልጣናትም ከአይሁዳውያን ጎን ተሰልፈው ነበሩ። ይሖዋ ለሕዝቡ ታላቅ ድል ሰጣቸው። ይሖዋ የሕዝቦቹ ጠላቶች ሙሉ በሙሉ ድል እንዲመቱ በማድረግ በሕዝቡ ላይ ዳግመኛ ጥቃት እንዳይሰነዘር እንዳደረገ ጥርጥር የለውም። *አስ. 9:1-6

27 ከዚህም በላይ የዚያ ክፉ ሰው ማለትም የሐማ አሥር ልጆች በሕይወት እያሉ መርዶክዮስ የሐማን ቤት ልቆጣጠር ቢል ለሕይወቱ የሚያሰጋ ይሆናል። ስለዚህ እነሱም ተገደሉ። (አስ. 9:7-10) አምላክ ቀደም ብሎ የሕዝቦቹ ጠላቶች የሆኑት ክፉዎቹ አማሌቃውያን ከምድር ገጽ እንደሚጠፉ ትንቢት ተናግሮ ስለነበር የሐማ ቤተሰብ ሲደመሰስ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜውን አገኘ። (ዘዳ. 25:17-19) ጥፋት ከተፈረደበት የአማሌቅ ብሔር ውስጥ በወቅቱ በሕይወት የነበሩት የሐማ ልጆች ሳይሆኑ አይቀሩም።

28, 29. (ሀ) ይሖዋ አስቴርም ሆነች ሕዝቧ በጦርነት እንዲካፈሉ የፈቀደው ለምንድን ነው? (ለ) አስቴር ከተወችው ምሳሌ ምን እንማራለን?

28 አስቴር ገና በወጣትነቷ በጣም ከባድ ኃላፊነት መሸከም ግድ ሆኖባት ነበር፤ ይህች ወጣት ጦርነትንና የሞት ፍርድ ማስፈጸምን የሚመለከቱ ንጉሣዊ አዋጆችን ከማውጣት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ማከናወን ነበረባት። ይህ ቀላል እንዳልነበር ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ የእስራኤል ብሔር እንዲጠፋ የይሖዋ ፈቃድ አልነበረም፤ ምክንያቱም የሰው ዘር ብቸኛ ተስፋ የሆነው መሲሕ የሚመጣው ከዚህ ብሔር ነበር! (ዘፍ. 22:18) ዛሬ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች፣ መሲሑ ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ተከታዮቹ በጦርነት እንዳይካፈሉ መከልከሉን ማወቃቸው ያስደስታቸዋል።—ማቴ. 26:52

29 ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ጦርነት ይካፈላሉ፤ ሰይጣን በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ለማጥፋት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቆርጦ ተነስቷል። (2 ቆሮንቶስ 10:3, 4ን አንብብ።) አስቴርን የመሰለች ምሳሌ ማግኘታችን ምንኛ በረከት ነው! እኛም እንደ እሷ በጥበብና በትዕግሥት ሌሎችን ለማሳመን በመጣር እንዲሁም ደፋሮች በመሆንና ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ከአምላክ ሕዝቦች ጎን በፈቃደኝነት በመቆም እምነት እንዳለን እናሳይ።

^ አን.26 ንጉሡ፣ አይሁዳውያን በጠላቶቻቸው ላይ የተቀዳጁትን ድል እንዲያጠናቅቁ ተጨማሪ ቀን ፈቀደላቸው። (አስ. 9:12-14) በዛሬው ጊዜም እንኳ አይሁዳውያን በየዓመቱ አዳር በተባለው ወር ላይ ይህን ድል ያገኙበትን ቀን ያከብራሉ፤ ይህ ወር በየካቲት ወር መገባደጃና በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ይውላል። ይህ በዓል ፉሪም ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ስያሜውን ያገኘው ሐማ እስራኤላውያንን ለመደምሰስ ከጣለው ዕጣ ነው።