ምዕራፍ አሥራ ሁለት
አምላኩ አጽናንቶታል
1, 2. ኤልያስ ፈጽሞ ሊረሳው በማይችለው በዚያ ታሪካዊ ዕለት ምን ነገር ተከናወነ?
ኤልያስ፣ ሰማዩ ይበልጥ እየጨላለመ ቢመጣም በዝናቡ ውስጥ መሮጡን አላቆመም። ኢይዝራኤል ለመድረስ ገና ብዙ መንገድ ይቀረዋል፤ በዚያ ላይ ደግሞ ኤልያስ በዕድሜ የገፋ ሰው ነው። ያም ሆኖ የይሖዋ ኃይል በእሱ ላይ ስለወረደ ምንም ዓይነት የድካም ስሜት ሳይታይበት መሮጡን ተያይዞታል። ጭራሽ፣ አክዓብ የተቀመጠበትን የቤተ መንግሥት ሠረገላ የሚጎትቱትን ፈረሶች ቀድሟቸው ሄደ! ኤልያስ ከዚህ በፊት እንደዚህ ያለ ብርታት አግኝቶ እንደማያውቅ ጥርጥር የለውም።—1 ነገሥት 18:46ን አንብብ።
2 አሁን ኤልያስ በረጅሙ መንገድ ላይ ብቻውን እየገሰገሰ ነው። ኤልያስ በዕለቱ የተፈጸመውን ፈጽሞ ሊረሳ የማይችል ክንውን እያሰበና የሚወርድበትን ዝናብ ከፊቱ ላይ እየጠረገ ሲሮጥ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ይህ ቀን የኤልያስ አምላክ የሆነው ይሖዋ ታላቅ ድል ያገኘበትና እውነተኛው አምልኮ ከፍ ከፍ ያለበት ዕለት ነው። ኤልያስ በጣም ርቆ በመሄዱና አካባቢው በጭጋግ በመሸፈኑ የተነሳ ይሖዋ በእሱ ተጠቅሞ ተአምራዊ በሆነ መንገድ የበኣልን አምልኮ ድባቅ የመታበት የቀርሜሎስ ተራራ ከዓይኑ ተሰውሯል። በመቶዎች የሚቆጠሩ የበኣል ነቢያት በክፋት የተሞሉ አታላዮች መሆናቸው የተጋለጠ ከመሆኑም በላይ የሚገባቸውን የሞት ቅጣት ተቀብለዋል። ከዚያም ኤልያስ ለሦስት ዓመት ተኩል ምድሪቱን ያጠቃው ድርቅ እንዲያከትም ወደ ይሖዋ ጸለየ። ዝናቡም መጣል ጀመረ!—1 ነገ. 18:18-45
3, 4. (ሀ) ኤልያስ ወደ ኢይዝራኤል እየተጓዘ ሳለ አንድ ለውጥ እንደሚመጣ ተስፋ አድርጎ ሊሆን ይችላል የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
3 ኤልያስ እስከ ኢይዝራኤል ድረስ ያለውን 30 ኪሎ ሜትር የሚሆን መንገድ በዝናብ እየተደበደበ በሚሮጥበት ጊዜ አንድ ትልቅ ለውጥ እንደሚመጣ ተስፋ ሳያደርግ አይቀርም። መቼም አክዓብ መለወጥ አለበት! ቀደም ሲል የተፈጸሙትን ነገሮች መመልከቱ የበኣል አምልኮን እርግፍ አድርጎ እንዲተው፣ የንግሥት ኤልዛቤልን ድርጊት እንዲያስቆምና የይሖዋን አገልጋዮች ከማሳደድ እንዲቆጠብ ሊያነሳሳው እንደሚገባ ግልጽ ነው።
4 ማናችንም ብንሆን ያሰብነው ነገር እየተሳካ እንዳለ ሲሰማን ተስፋችን እንደሚለመልም የታወቀ ነው። ሕይወታችን ይበልጥ እየተቃናልን እንደሚሄድ አልፎ ተርፎም ራስ ምታት ከሆኑብን ችግሮች ሙሉ በሙሉ እንደምንገላገል ይሰማን ይሆናል። ኤልያስ እንዲህ ተሰምቶት ከነበረ ምንም አያስደንቅም፤ ምክንያቱም እሱም ቢሆን “እንደ እኛው ዓይነት ስሜት ያለው ሰው” ነው። (ያዕ. 5:17) እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፣ ኤልያስ እንዳሰበው ከችግሮቹ አይገላገልም። እንዲያውም ኤልያስ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በከፍተኛ ፍርሃትና በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተውጦ ሞቱን እስከመመኘት ይደርሳል። ለመሆኑ እንዲህ የሚሰማው ምን ቢያጋጥመው ነው? ይሖዋ ይህ ነቢይ እምነቱን እንዲያጠናክርና ድፍረቱን መልሶ እንዲያገኝ የሚረዳውስ እንዴት ነው? እስቲ እነዚህን ጉዳዮች በዝርዝር እንመልከት።
ያልተጠበቀ ሁኔታ ተከሰተ
5. አክዓብ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ የተከናወኑትን ነገሮች ከተመለከተ በኋላ ለይሖዋ አምላክ ክብር መስጠት እንዳለበት ትምህርት አግኝቶ ነበር? ይህን እንዴት እናውቃለን?
5 አክዓብ ከቀርሜሎስ ተነስቶ ኢይዝራኤል ወደሚገኘው ቤተ መንግሥቱ ሲመለስ በሕይወቱ ውስጥ ለውጥ እንዳደረገ የሚያሳይ እርምጃ ይወስድ ይሆን? ዘገባው “አክዓብ በዚህ ጊዜ፣ ኤልያስ ያደረገውን በሙሉ፣ ነቢያቱንም ሁሉ እንዴት በሰይፍ እንዳስገደላቸው ለኤልዛቤል ነገራት” ይላል። (1 ነገ. 19:1) አክዓብ በዕለቱ ስለተከናወኑት ነገሮች ሲናገር የኤልያስ አምላክ የሆነውን ይሖዋን እንዳልጠቀሰ ልብ በል። ሥጋዊ አስተሳሰብ የነበረው አክዓብ በዕለቱ የተከናወኑትን ተአምራዊ ነገሮች የተመለከታቸው ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ብቻ ይኸውም ‘ኤልያስ እንዳደረጋቸው’ አድርጎ ነበር። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አክዓብ ለይሖዋ አምላክ ክብር መስጠት እንዳለበት ትምህርት አላገኘም። የበቀል መንፈስ የተጠናወታት ሚስቱስ ምን ታደርግ ይሆን?
6. ኤልዛቤል ለኤልያስ ምን መልእክት ላከችበት? ምን ማለቷስ ነበር?
6 ኤልዛቤል ኤልያስ ያደረገውን ስትሰማ ደሟ ፈላ! ከዚያም በንዴት ፊቷ ተለዋውጦ “ነገ በዚህ ሰዓት ያንተንም ነፍስ ከእነዚያ እንደ አንዱ ነፍስ ሳላደርጋት ብቀር አማልክት እንዲህ ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጡብኝ” የሚል መልእክት ላከችበት። (1 ነገ. 19:2) ይህ ዛቻ እሱን ለመግደል ቆርጣ መነሳቷን የሚያሳይ ነበር። በሌላ አባባል ‘የበኣል ነቢያቴን እንደገደልክ እኔም በነገው ዕለት አንተን ሳልገድል ብቀር ሞቻለሁ’ ብላ መዛቷ ነበር። ዶፍ በሚወርድበት በዚያ ሌሊት አንድ ሰው ኤልያስን ከእንቅልፉ ሲቀሰቅሰው በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ፤ የንግሥቲቱ መልእክተኛ ወደ እሱ የሄደው ምሥራች ሊያበስረው ሳይሆን ሽብር የሚለቅ መልእክት ሊነግረው ነው። ታዲያ በዚህ ጊዜ ኤልያስ ምን ተሰማው?
በፍርሃትና በተስፋ መቁረጥ ስሜት መዋጥ
7. ኤልያስ የኤልዛቤልን ዛቻ ሲሰማ ምን ተሰማው? ምንስ አደረገ?
7 ኤልያስ ከበኣል አምልኮ ጋር የሚደረገው ፍልሚያ እንዳበቃ በማሰብ ተደስቶ ከነበረ ይህን ዛቻ በሰማበት ቅጽበት ተስፋው እንደ ጉም በንኖ እንደጠፋ ጥርጥር የለውም። ኤልዛቤል የተከናወኑትን ነገሮች ብትሰማም ከአቋሟ ፍንክች አላለችም። ከዚህ ቀደም በርካታ ታማኝ ነቢያትን አስገድላለች፤ አሁን ደግሞ ኤልያስ ይህ ዕጣ ይጠብቀዋል። ኤልያስ የኤልዛቤልን ዛቻ ሲሰማ ምን ተሰማው? መጽሐፍ ቅዱስ ‘ኤልያስ ፈርቶ እንደነበር’ ይገልጻል። ምናልባት ኤልያስ፣ ኤልዛቤል እንዴት ባለ አሰቃቂ ሁኔታ ልትገድለው እንደምትችል በዓይነ ሕሊናው ታይቶት ይሆን? እንዲህ ያሉ ሐሳቦችን ሲያወጣና ሲያወርድ ከነበረ ወኔ ቢከዳው ምንም አያስገርምም። ምንም ሆነ ምን ኤልያስ “ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ሸሸ።”—1 ነገ. 18:4፤ 19:3
ፍርሃት እንዳያሽመደምደን ከፈለግን አእምሯችን ከፊታችን በተጋረጠው አደጋ ላይ እንዲያተኩር ማድረግ የለብንም
8. (ሀ) ጴጥሮስ ያጋጠመው ችግር ከኤልያስ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? (ለ) ከጴጥሮስና ከኤልያስ ምን ትምህርት እናገኛለን?
ማቴዎስ 14:30ን አንብብ።) እኛም ከጴጥሮስና ከኤልያስ ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን። ፍርሃት እንዳያሽመደምደን ከፈለግን አእምሯችን ከፊታችን በተጋረጠው አደጋ ላይ እንዲያተኩር ማድረግ የለብንም። ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ትኩረታችን ማረፍ ያለበት የተስፋችንና የብርታታችን ምንጭ በሆነው አምላክ ላይ ነው።
8 ከእምነት ሰዎች መካከል በፍርሃት የተሸነፈው ኤልያስ ብቻ አይደለም። ከብዙ ዘመናት በኋላ የኖረው ሐዋርያው ጴጥሮስም ተመሳሳይ ችግር አጋጥሞታል። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት ኢየሱስ በውኃ ላይ እየተራመደ ወደ እሱ እንዲመጣ ባደረገው ጊዜ ሐዋርያው “ማዕበሉን ሲያይ ፈራ፤” ከዚያም መስጠም ጀመረ። (“በቅቶኛል”
9. ኤልያስ ያደረገው ጉዞ ምን ይመስል እንደነበረና በሚሸሽበት ወቅት ምን ስሜት አድሮበት ሊሆን እንደሚችል ግለጽ።
9 ኤልያስ በጣም ስለፈራ በስተ ደቡብ ምዕራብ 150 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘውና በይሁዳ ደቡባዊ ድንበር አቅራቢያ ወዳለችው ወደ ቤርሳቤህ ከተማ ሸሸ። ቤርሳቤህ እንደደረሰም አገልጋዩን በዚያ ትቶት ብቻውን ወደ ምድረ በዳ ሄደ። ዘገባው ኤልያስ “የአንድ ቀን መንገድ” እንደተጓዘ ስለሚናገር ጉዞውን የጀመረው ገና በማለዳ እንደሆነ መገመት እንችላለን፤ ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ኤልያስ በዚህ ወቅት ምንም ስንቅ አልያዘም። በጭንቀትና በፍርሃት የተዋጠው ይህ ነቢይ ወጣ ገባ የሆነውን ጭር ያለ መንገድ ይዞ በዚያ ጠራራ ፀሐይ ማዝገም ጀምሯል። አናት የሚበሳው ፀሐይ ቀስ በቀስ እየበረደ ሲሄድና ጀንበሯ ስታዘቀዝቅ ኤልያስም ጉልበቱ እየዛለ መጣ። ስለሆነም ዝልፍልፍ ብሎ በአቅራቢያው ባገኘው አንድ የክትክታ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ በዚያ ጠፍ ምድረ በዳ ያለው ብቸኛ መጠለያ ይህ ዛፍ ነበር።—1 ነገ. 19:4
10, 11. (ሀ) ኤልያስ ወደ ይሖዋ ያቀረበው ጸሎት ምን ትርጉም አለው? (ለ) በአንቀጹ ላይ የሰፈሩት ጥቅሶች ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች በሐዘን በተደቆሱበት ወቅት ምን ተሰምቷቸው እንደነበር ይገልጻሉ?
10 ኤልያስ በከፍተኛ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ተውጦ ወደ ይሖዋ ጸለየ። “እኔ ከቀደሙት አባቶቼ አልበልጥም” በማለት እንዲሞት ለመነ። በመቃብር ውስጥ ያሉት የቀድሞ አባቶቹ አፈር እንደሆኑና ለማንም ምንም የሚጠቅም ነገር ማከናወን እንደማይችሉ አሳምሮ ያውቃል። (መክ. 9:10) ስለዚህ ከእነሱ ምንም እንደማይሻል ተሰምቶታል። በመሆኑም “በቅቶኛል” በማለት በምሬት መናገሩ ምንም አያስገርምም። ‘የእኔ በሕይወት መኖር ምን ጥቅም አለው?’ የሚል ስሜት ሳያድርበት አልቀረም።
11 አንድ የአምላክ አገልጋይ ይህን ያህል ተስፋ መቁረጡ ሊያስገርመን ይገባል? በፍጹም። በሐዘን በመደቆሳቸው የተነሳ ሞትን የተመኙ በርካታ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝገበው የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ርብቃ፣ ያዕቆብ፣ ሙሴና ኢዮብ ይገኙበታል።—ዘፍ. 25:22፤ 37:35፤ ዘኍ. 11:13-15፤ ኢዮብ 14:13
12. የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሲያድርብህ የኤልያስን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው?
2 ጢሞ. 3:1) አንተም እንዲህ ያለ አስጨናቂ ሁኔታ ካጋጠመህ የኤልያስን ምሳሌ በመከተል የውስጥህን ስሜት አውጥተህ ለአምላክ ንገረው። ደግሞም ይሖዋ “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” መሆኑን አስታውስ። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4ን አንብብ።) ታዲያ ይሖዋ ኤልያስን አጽናንቶት ይሆን?
12 የምንኖረው ‘ለመቋቋም በሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን’ ውስጥ በመሆኑ በርካታ ሰዎች ሌላው ቀርቶ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችም ጭምር የተስፋ መቁረጥ ስሜት ቢሰማቸው የሚያስደንቅ አይሆንም። (ይሖዋ ነቢዩን አበረታው
13, 14. (ሀ) ይሖዋ መልአክ በመላክ ችግር ላይ ለወደቀው የእሱ ነቢይ ፍቅራዊ አሳቢነት ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ የአቅም ገደቦቻችንን ጨምሮ ስለ እያንዳንዳችን ሁሉንም ነገር እንደሚያውቅ መገንዘባችን የሚያጽናናን እንዴት ነው?
13 ይሖዋ ከሰማይ ሆኖ በጣም የሚወደውንና ሞቱን እየተመኘ የነበረውን ይህን ነቢይ ምድረ በዳ ውስጥ ባለች አንዲት ዛፍ ሥር ተቀምጦ ሲመለከተው ምን የተሰማው ይመስልሃል? መልሱን መገመት አያስፈልገንም። ኤልያስ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወስዶት ሳለ ይሖዋ አንድ መልአክ ላከ። መልአኩም ኤልያስን ቀስ ብሎ ነካ በማድረግ ከቀሰቀሰው በኋላ “ተነሥና ብላ” አለው። መልአኩ በደግነት ትኩስ ዳቦና ውኃ ስላቀረበለት ኤልያስ ተነስቶ በላ እንዲሁም ጠጣ። ኤልያስ ከበላ በኋላ መልአኩን አመስግኖታል ብለህ ታስባለህ? ዘገባው የሚናገረው ነቢዩ ከበላና ከጠጣ በኋላ ተመልሶ እንደተኛ ብቻ ነው። ምናልባት በተስፋ መቁረጥ ስሜት ከመዋጡ የተነሳ መናገር እንኳ ተስኖት ይሆን? ያም ሆነ ይህ መልአኩ ኤልያስን በድጋሚ ቀሰቀሰው፤ በዚህ ወቅት ጎህ ሳይቀድ አይቀርም። አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ “ተነሥና ብላ” በማለት እንዲበላ ገፋፋው፤ በተጨማሪም መልአኩ “ሩቅ መንገድ ስለምትሄድ” የሚል ሐሳብ መናገሩ ትኩረት የሚስብ ነው።—1 ነገ. 19:5-7
14 መልአኩ፣ አምላክ ማስተዋል ስለሰጠው ኤልያስ ወዴት እንደሚሄድ አውቆ ነበር። ከዚህም ባሻገር ይህ መልአክ ኤልያስ ከፊቱ የሚጠብቀውን ረጅም መንገድ በራሱ ኃይል ብቻ ሊወጣው እንደማይችል ተረድቶ ነበር። ስለ ግቦቻችንና ስላሉብን የአቅም ገደቦች ከእኛ በተሻለ የሚያውቀውን አምላክ ማገልገል እንዴት የሚያጽናና ነው! (መዝሙር 103:13, 14ን አንብብ።) ታዲያ ኤልያስ ምግብ መብላቱ የጠቀመው እንዴት ነው?
15, 16. (ሀ) ኤልያስ ይሖዋ የመገበው ምግብ ምን እንዲያደርግ አስችሎታል? (ለ) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ አገልጋዮቹን ለማበርታት የሚጠቀምበትን መንገድ በአድናቆት መመልከት ያለብን ለምንድን ነው?
15 ታሪኩ እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “ተነሥቶ በላ፤ ጠጣም፤ በምግቡም ብርታት አግኝቶ ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ኮሬብ እስኪደርስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ተጓዘ።” (1 ነገ. 19:8) ኤልያስ እሱ ከኖረበት ዘመን ከስድስት መቶ ዓመታት በፊት ይኖር እንደነበረው እንደ ሙሴ እንዲሁም እሱ ከኖረበት ዘመን ከአንድ ሺህ ዓመታት በኋላ እንደኖረው እንደ ኢየሱስ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾሟል። (ዘፀ. 34:28፤ ሉቃስ 4:1, 2) ኤልያስ አንድ ጊዜ የተመገበው ምግብ ችግሮቹን በሙሉ አስወግዶለታል ማለት ባይሆንም ተአምራዊ በሆነ መንገድ ብርታት ሰጥቶታል። በዕድሜ የገፋው ይህ ነቢይ ምንም ዓይነት የእግር መንገድ በሌለበት በዚያ ምድረ በዳ ለቀናት ብሎም ለሳምንታት በአጠቃላይ ለአንድ ወር ተኩል ገደማ ብቻውን ሲኳትን በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ!
ማቴ. 4:4) ከአምላክ ቃልና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተመሠረቱ ሌሎች ጽሑፎች ስለ አምላክ መማራችን መንፈሳዊ ብርታት እንድናገኝ ያደርገናል። እንዲህ የመሰለ መንፈሳዊ ምግብ መመገባችን ችግሮቻችንን በሙሉ ባያስወግድልንም በዚህ መንገድ ካልሆነ በስተቀር ልንወጣቸው የማንችላቸውን ፈተናዎች በጽናት እንድንቋቋም ይረዳናል። በተጨማሪም ወደ “ዘላለም ሕይወት” ይመራናል።—ዮሐ. 17:3
16 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ አገልጋዮቹን በሥጋዊ ምግብ አማካኝነት ተአምራዊ ኃይል እንዲያገኙ ባያደርግም ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊ በሆነ ሌላ መንገድ ያበረታቸዋል። ለአገልጋዮቹ መንፈሳዊ ምግብ ያቀርባል። (17. ኤልያስ ወዴት ሄደ? ይህ ቦታስ ታሪካዊ ነበር የምንለው ለምንድን ነው?
17 ኤልያስ ወደ 320 የሚጠጋ ኪሎ ሜትር ከተጓዘ በኋላ ኮሬብ ተራራ ደረሰ። ከብዙ ዘመናት በፊት ይሖዋ አምላክ በሚነድ ቁጥቋጦ ውስጥ በአንድ መልአክ አማካኝነት ለሙሴ የተገለጠለትና በኋላም ለእስራኤላውያን ሕጉን የሰጣቸው በዚህ ስፍራ ስለሆነ ይህ ቦታ ታሪካዊ ነበር። ኤልያስ አንድ ዋሻ ሲያገኝ እዚያ ውስጥ ገብቶ አረፍ አለ።
ይሖዋ ነቢዩን ያጽናናበትና ያበረታበት መንገድ
18, 19. (ሀ) የይሖዋ መልእክተኛ የሆነው መንፈሳዊ ፍጡር ለኤልያስ ምን ጥያቄ አቀረበለት? እሱስ ምን ምላሽ ሰጠ? (ለ) ከኤልያስ አነጋገር መረዳት እንደሚቻለው ተስፋ እንዲቆርጥ ያደረጉትን ሦስት ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
18 ኤልያስ በኮሬብ ሳለ የይሖዋ “ቃል” (ምናልባትም ይህን ቃል ይዞ የመጣው መንፈሳዊ ፍጡር የሆነ አንድ መልእክተኛ ሊሆን ይችላል) “ኤልያስ ሆይ፤ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” የሚል አጭር ጥያቄ አቀረበለት። ጥያቄው ለስለስ ባለ መንገድ የቀረበ ሳይሆን አይቀርም፤ ምክንያቱም ኤልያስ የልቡን አውጥቶ ለመናገር ጥሩ አጋጣሚ እንደተከፈተለት ተሰምቶታል። እሱም የተሰማውን በሙሉ ተናግሯል! እንዲህ ብሏል፦ “እኔ ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ እስራኤላውያን ኪዳንህን ትተዋል፤ መሠዊያዎችህን አፍርሰዋል፤ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና። የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ፤ አሁንም እኔን ለመግደል ይፈልጋሉ።” (1 ነገ. 19:9, 10) ከዚህ አነጋገሩ መረዳት እንደሚቻለው ኤልያስን ተስፋ እንዲቆርጥ ያደረጉት ቢያንስ ሦስት ምክንያቶች አሉ።
19 በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኤልያስ ልፋቱ መና እንደቀረ ተሰምቶታል። ለዓመታት የአምላክን ቅዱስ ስምና አምልኮ በማስቀደም ይሖዋን የማገልገል ከፍተኛ ‘ቅንዓት’ እንዳለው ቢያሳይም ሁኔታዎቹ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሱ እንደሄዱ ተሰምቶታል። ሕዝቡ አሁንም እምነት የለሽና ዓመፀኛ ሲሆን በአንጻሩ ደግሞ የሐሰት አምልኮ በጣም እየተስፋፋ ነበር። በሁለተኛ ደረጃ፣ ኤልያስ ብቻውን እንደቀረ ተሰምቶታል። በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች መካከል የተረፈው እሱ ብቻ ይመስል “የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ” በማለት ተናግሯል። በሦስተኛ ደረጃ፣ ኤልያስ ፍርሃት አድሮበታል። እንደ እሱ ይሖዋን ያገለግሉ ከነበሩት ነቢያት ውስጥ አብዛኞቹ ስለተገደሉ እሱም የእነሱ ዕጣ እንደማይቀርለት እርግጠኛ ነበር። ይህን ስሜቱን አውጥቶ መናገር ለኤልያስ ቀላል ላይሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ ኩራትም ሆነ ኀፍረት ስሜቱን አውጥቶ ከመናገር ወደኋላ እንዲል አላደረገውም። የልቡን አውጥቶ ለአምላክ በጸሎት በመናገር ረገድ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ ጥሩ ምሳሌ ትቷል።—መዝ. 62:8
20, 21. (ሀ) ኤልያስ በኮሬብ ተራራ በሚገኘው ዋሻ ደጃፍ ላይ ሆኖ ምን እንደተመለከተ ግለጽ። (ለ) ኤልያስ የይሖዋን ኃይል የሚያሳዩ ትዕይንቶችን መመልከቱ ምን እንዲገነዘብ ረድቶታል?
20 ይሖዋ የኤልያስን ፍርሃትና ጭንቀት ለማስወገድ ምን አደረገ? መልአኩ 1 ነገ. 19:11, 12
ኤልያስን በዋሻው መግቢያ ላይ እንዲቆም ነገረው። ኤልያስ ቀጥሎ ምን እንደሚከናወን ባያውቅም እንደታዘዘው አደረገ። በድንገት ኃይለኛ ነፋስ ነፈሰ! በዚህ ጊዜ ጆሮ የሚያደነቁር ድምፅ ተሰምቶ መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ነፋሱ በጣም ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ተራሮቹና ዐለቶቹ ተሰነጣጥቀዋል። ኤልያስ በአንድ እጁ ነፋሱ ፀጉራም ካባውን ከላዩ ላይ ገፍፎ እንዳይወስድበት ሙጭጭ አድርጎ ይዞ በሌላኛው እጁ ዓይኑን ለመከለል ሲሞክር በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ከዚያም የመሬት መንቀጥቀጥ አካባቢውን አናወጠው፤ በዚህ ወቅት ኤልያስ ሚዛኑን ለመጠበቅ ምን ያህል ትግል እንደሚያደርግ ለማሰብ ሞክር! ከዚያም ኤልያስ ገና ሳይረጋጋ ኃይለኛ የእሳት ወላፈን አካባቢውን ገረፈው፤ በመሆኑም ኤልያስ ራሱን ከእሳቱ ወላፈን ለማዳን ዋሻው ውስጥ ዘሎ ገባ።—21 ሦስቱም ሁኔታዎች በተከሰቱበት ወቅት ይሖዋ በእነዚያ አስደናቂ የተፈጥሮ ኃይሎች ውስጥ እንዳልነበር ዘገባው ይነግረናል። ኤልያስ፣ ይሖዋ አምላኪዎቹ “ደመና ጋላቢ” ወይም ዝናብ አምጪ እንደሆነ በማሰብ ክብር እንደሚሰጡት እንደ በኣል ያለ በተፈጥሮ ኃይሎች ውስጥ የሚገኝ ምናብ የወለደው አምላክ እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። ይሖዋ በጣም አስደናቂ የሆኑት የተፈጥሮ ኃይሎች ሁሉ ምንጭ ከመሆኑም በላይ እሱ ከሠራው ከማንኛውም ነገር እጅግ የላቀ ነው። ግዑዝ የሆኑት ሰማያትም እንኳ ሊይዙት አይችሉም! (1 ነገ. 8:27) ታዲያ ኤልያስ ይህን ሁሉ መመልከቱ የጠቀመው እንዴት ነው? ኤልያስ ምን ያህል ፈርቶ እንደነበር አስታውስ። ታዲያ ኤልያስ፣ በፈለገው ጊዜ ሊጠቀምበት የሚችል ይህ ነው የማይባል ኃይል ያለው ይሖዋ ከጎኑ እያለለት አክዓብንም ሆነ ኤልዛቤልን የሚፈራበት ምን ምክንያት አለ?—መዝሙር 118:6ን አንብብ።
22. (ሀ) ‘ለስለስ ያለው ድምፅ’ ኤልያስ ዋጋ ቢስ አለመሆኑን እንዲገነዘብ የረዳው እንዴት ነው? (ለ) ‘ለስለስ ያለው ድምፅ’ ምንጭ ማን ሊሆን ይችላል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
22 እሳቱ እንዳለፈ ጸጥታ ሰፈነ፤ ከዚያም ኤልያስ “ለስለስ ያለ ድምፅ” ሰማ። ድምፁም ኤልያስ ስሜቱን በድጋሚ እንዲገልጽ የሚያበረታታ ነበር፤ ስለሆነም ኤልያስ ያስጨነቀውን ነገር ለሁለተኛ ጊዜ ግልጥልጥ አድርጎ ተናገረ። * ምናልባትም እንዲህ ማድረጉ ይበልጥ ቀለል እንዲለው ሳያደርገው አልቀረም። ያም ሆኖ ‘ለስለስ ያለው ድምፅ’ ቀጥሎ የተናገረው ሐሳብ ኤልያስን ይበልጥ አጽናንቶት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ይሖዋ፣ ኤልያስ እሱ እንዳሰበው ዋጋ ቢስ አለመሆኑን እንዲገነዘብ ረዳው። ይህን ያደረገው እንዴት ነው? አምላክ የበኣል አምልኮን ከእስራኤል ምድር ለማስወገድ ከሚደረገው ጦርነት ጋር በተያያዘ ወደፊት ምን ለማድረግ እንዳሰበ ገለጸለት። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው የአምላክ ዓላማ አንዳች የሚገታው ነገር ሳይኖር ወደፊት በመገስገስ ላይ ስለሆነ የኤልያስ ልፋት ከንቱ ሆኖ አልቀረም። ከዚህም በላይ ይሖዋ ለኤልያስ አንዳንድ ዝርዝር መመሪያዎችን በመስጠት እንደገና ወደ ሥራው እንዲመለስ ስላደረገው ይህ ነቢይ አሁንም ቢሆን በይሖዋ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተው ሚና አለ።—1 ነገ. 19:12-17
23. ይሖዋ፣ ኤልያስ የተሰማውን የብቸኝነት ስሜት እንዲወጣ ለመርዳት ምን ሁለት ነገሮች አደረገ?
23 ኤልያስ የተሰማው የብቸኝነት ስሜትስ መፍትሔ አግኝቶ ይሆን? ይሖዋ ይህን ችግር ለመፍታት ሁለት ነገሮችን አድርጓል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ከጊዜ በኋላ እሱን የሚተካውን ኤልሳዕን ነቢይ አድርጎ እንዲቀባው ለኤልያስ ነገረው። ከኤልያስ በዕድሜ የሚያንሰው ይህ ሰው የኤልያስ የሥራ ባልደረባና ረዳት በመሆን ለብዙ ዓመታት ሊያገለግል ነው። በእርግጥም ይህ ለችግሩ ትክክለኛ መፍትሔ ነው! በሁለተኛ ደረጃ፣ ይሖዋ የሚከተለውን በጣም አስደሳች ዜና አበሰረው፦ “እኔም ጕልበታቸው ለበኣል ያልተንበረከከውንና አፋቸው ምስሉን ያልሳመውን ሰባት ሺህ ሰዎች በእስራኤል አስቀራለሁ [“አስቀርቼያለሁ፣” NW]።” (1 ነገ. 19:18) ለካስ ኤልያስ ብቻውን አልነበረም! በኣልን ለማምለክ ፈቃደኛ ያልሆኑ በሺህ የሚቆጠሩ ታማኝ ሰዎች እንዳሉ ሲሰማ በጣም ተደስቶ መሆን አለበት። በዚያ የጨለማ ዘመን ኤልያስ ይሖዋን በታማኝነት ማገልገሉን መቀጠሉ እነዚህ ሰዎች የእሱን ምሳሌ እንዲከተሉ ያነሳሳቸዋል። ኤልያስ በይሖዋ መልእክተኛ አማካኝነት የአምላኩን “ለስለስ ያለ ድምፅ” መስማቱ ልቡ በጥልቅ እንዲነካ ሳያደርገው አልቀረም።
ዛሬም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲመራን የምንፈቅድ ከሆነ ኤልያስ እንደሰማው ዓይነት “ለስለስ ያለ ድምፅ” ሆኖልናል ሊባል ይችላል
24, 25. (ሀ) በዛሬው ጊዜ የይሖዋን “ለስለስ ያለ ድምፅ” መስማት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ኤልያስ ይሖዋ የሰጠው ማጽናኛ እንዳበረታታው እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
24 እኛም እንደ ኤልያስ በአምላክ የፍጥረት ሥራዎች ላይ በግልጽ የሚታዩትን ታላላቅ የተፈጥሮ ኃይሎች ስንመለከት ልንደመም እንችላለን፤ ደግሞም መደመማችን ተገቢ ነው። ፍጥረት የፈጣሪን ኃይል በግልጽ ያንጸባርቃል። (ሮም 1:20) ይሖዋ ዛሬም ቢሆን ገደብ የሌለው ኃይሉን በመጠቀም ታማኝ አገልጋዮቹን መርዳት ያስደስተዋል። (2 ዜና 16:9) ይሁን እንጂ አምላክ እኛን ለማናገር በዋነኝነት የሚጠቀመው ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ነው። (ኢሳይያስ 30:21ን አንብብ።) በሌላ አባባል ዛሬም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲመራን የምንፈቅድ ከሆነ የአምላክ ቃል ኤልያስ እንደሰማው ዓይነት “ለስለስ ያለ ድምፅ” ሆኖልናል ሊባል ይችላል። ይሖዋ ውድ በሆነው ቃሉ አማካኝነት እርማት ይሰጠናል፣ ያበረታታናል እንዲሁም እንደሚወደን ያረጋግጥልናል።
25 ታዲያ ኤልያስ ይሖዋ በኮሬብ ተራራ ላይ በሰጠው ማጽናኛ ተበረታቷል? ምን ጥያቄ አለው! ወዲያውኑ ወደ ሥራው በመመለስ እንደ ድሮው የሐሰት አምልኮ በክፋት የተሞላ መሆኑን በድፍረትና በታማኝነት ማጋለጥ ጀመረ። እኛም በተመሳሳይ በመንፈስ መሪነት ከተጻፈው የአምላክ ቃል ማለትም ‘ከቅዱሳን መጻሕፍት የምናገኘውን መጽናኛ’ በቁም ነገር የምንመለከት ከሆነ ኤልያስን በእምነቱ ልንመስለው እንችላለን።—ሮም 15:4
^ አን.22 የዚህ “ለስለስ ያለ ድምፅ” ምንጭ በ1 ነገሥት 19:9 ላይ የተጠቀሰውን የይሖዋን “ቃል” እንዲያደርስ የተላከው መንፈሳዊ አካል ራሱ ሳይሆን አይቀርም። በቁጥር 15 (NW) ላይ ይህ መንፈሳዊ አካል “ይሖዋ” ተብሎ ተጠርቷል። ይህም ይሖዋ እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ለመምራት የተጠቀመበትንና “ስሜ በርሱ ላይ ነው” በማለት የተናገረለትን መንፈሳዊ አካል ያስታውሰን ይሆናል። (ዘፀ. 23:21) እውነት ነው፣ ስለዚህ ጉዳይ በእርግጠኝነት መናገር አንችልም፤ ያም ሆኖ ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት “ቃል” ማለትም ለይሖዋ አገልጋዮች ልዩ ቃል አቀባይ ሆኖ እንዳገለገለ ልብ ማለት ይገባል።—ዮሐ. 1:1