ምዕራፍ አምስት
“ምግባረ መልካም ሴት”
1, 2. (ሀ) ሩት ምን እየሠራች ነበር? (ለ) ሩት የአምላክን ሕግና ሕዝቦቹን በተመለከተ ምን መልካም ነገር መገንዘብ ችላለች?
ሩት ቀኑን ሙሉ ስትሰበስብ ውላ በቆለለችው የገብስ ነዶ አጠገብ በርከክ ብላለች። ቀኑ ለዓይን ያዝ ማድረግ ጀምሯል፤ በቤተልሔም ዙሪያ ባሉት ማሳዎች ላይ ሲሠሩ የዋሉ በርካታ ሠራተኞች በአቅራቢያው ባለው ኮረብታ ላይ ወደምትገኘው ትንሽ ከተማ ማዝገም ጀምረዋል። ሩት ከማለዳ ጀምራ ቀኑን ሙሉ ያለ እረፍት ስትለፋ ስለዋለች ሰውነቷ እንደዛለ ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ፣ ገና ሥራዋን አልጨረሰችም፤ እህሉን ከገለባው ለመለየት በበትር መውቃት ጀመረች። ሥራው አድካሚ ቢሆንም ካሰበችው በላይ አስደሳች ቀን አሳልፋለች።
2 ይህች ወጣት መበለት የኋላ ኋላ ነገሮች እየተቃኑላት ይሆን? ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው ሩት ከአማቷ ላለመነጠልና የኑኃሚን አምላክ የሆነውን ይሖዋን ለማምለክ ቃል በመግባት ፈጽሞ ከኑኃሚን ላለመለየት ወስና ነበር። የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት የተነጠቁት ሩትና ኑኃሚን ከሞዓብ ምድር ወደ ቤተልሔም የመጡት አብረው ነው፤ ብዙም ሳይቆይ ሞዓባዊቷ ሩት በይሖዋ ሕግ ውስጥ መጻተኞችን ጨምሮ ድሆችን የሚጠቅምና ክብራቸውን የሚጠብቅ ዝግጅት እንዳለ አወቀች። አሁን ደግሞ በሕጉ ሥር የሚተዳደሩና በሕጉ የሚመሩ የይሖዋ ሕዝቦች ያላቸው መንፈሳዊ አመለካከት እንዲሁም ያሳዩአት ደግነት በሐዘን የተሰበረው ልቧ እንዲጠገን አደረገ።
3, 4. (ሀ) ቦዔዝ ሩትን ያበረታታት እንዴት ነው? (ለ) የኑሮ ውድነት ባለበት በዛሬው ጊዜ ሩት የተወችው ምሳሌ ሊጠቅመን የሚችለው እንዴት ነው?
3 እንዲህ ካሉት ሰዎች መካከል አንዱ ቦዔዝ ሲሆን ሩት እየቃረመች የነበረውም በዕድሜ ጠና ባለው በዚህ ባለጸጋ ሰው ማሳ ውስጥ ነበር። ዛሬም ልክ እንደ አባት ተንከባክቧታል። ቦዔዝ፣ አረጋዊቷን ኑኃሚንን በመንከባከቧና በእውነተኛው አምላክ በይሖዋ ክንፎች ጥላ ሥር ለመጠለል በመምረጧ ሩትን አመስግኗታል፤ እሷም ቦዔዝ የተናገራቸውን ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ቃላት ስትሰማ በውስጧ ደስ እንዳላት የታወቀ ነው።—ሩት 2:11-14ን አንብብ።
4 ያም ሆኖ ሩት የወደፊት ሕይወቷ ሳያሳስባት አልቀረም። ባልም ሆነ ልጅ የሌላት ድሃ የባዕድ አገር ሰው እንደመሆኗ መጠን ወደፊት ራሷንም ሆነ ኑኃሚንን ማስተዳደር የምትችለው እንዴት ነው? እህል በመቃረም ብቻ ኑሯቸውን መግፋት ይችሉ
ይሆን? ደግሞስ እሷ ራሷ ስታረጅ ማን ይጦራታል? ሩት እንዲህ ያሉ ሐሳቦች ቢያስጨንቋት የሚያስገርም አይሆንም። የኑሮ ውድነት ባለበት በዛሬው ጊዜም ብዙዎች ተመሳሳይ ነገሮች ያስጨንቋቸዋል። ሩት ያላት እምነት እንዲህ ዓይነቶቹን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንድትወጣ የረዳት እንዴት እንደሆነ ማወቃችን እኛም የእሷን ምሳሌ መከተል የምንችልባቸው ብዙ መንገዶች እንዳሉ ያስገነዝበናል።ቤተሰብን ‘ቤተሰብ’ የሚያሰኘው ምንድን ነው?
5, 6. (ሀ) ሩት በቦዔዝ እርሻ ውስጥ በቃረመችበት በመጀመሪያው ቀን ምን ያህል ተሳክቶላት ነበር? (ለ) ኑኃሚን ሩትን ስታያት ምን ተሰማት?
5 ሩት የቃረመችውን ገብስ ከወቃች በኋላ ስትሰፍረው አንድ የኢፍ መስፈሪያ ወይም 22 ሊትር ያህል ሆነ። ምናልባትም የሰበሰበችው እህል 14 ኪሎ ግራም ገደማ ሳይሆን አይቀርም! እህሉን በጨርቅ ቋጥራ በጭንቅላቷ በመሸከም ወደ ቤቷ ማዝገም ጀመረች፤ ወደ ቤተልሔም ስትደርስ ጨለምለም ብሎ ነበር።—ሩት 2:17
6 ኑኃሚን፣ የምትወዳት ምራቷ እንደተመለሰች ስታይ ተደሰተች፤ ሩት ይህን ያህል ገብስ ቃርማ መምጣቷን ስትመለከት ሳትገረም አልቀረችም። ሩት፣ ቦዔዝ ለሠራተኞቹ ካቀረበው ምሳ በልታ የተረፋትን ምግብም አምጥታ ነበር፤ ሁለቱ ሴቶች ይህን ምግብ ተካፍለው ራታቸውን በሉ። ከዚያም ኑኃሚን “ዛሬ የቃረምሽው ከየት ነው? የትስ ቦታ ስትሠሪ ዋልሽ? መልካም ነገር ያደረገልሽ ሰው የተባረከ ይሁን” አለቻት። (ሩት 2:19) ኑኃሚን አስተዋይ ስለነበረች ሩት የተሸከመችውን እህል ስትመለከት ለዚህች ወጣት መበለት ትኩረት የሰጣትና ደግነት ያሳያት ሰው እንዳለ መገንዘብ ችላ ነበር።
7, 8. (ሀ) ኑኃሚን ቦዔዝ ደግነት እንዲያሳይ ያነሳሳው ማን እንደሆነ ተሰምቷት ነበር? ለምንስ? (ለ) ሩት ለአማቷ ያላት ጽኑ ፍቅር እንዳልቀነሰ ያሳየችው እንዴት ነው?
7 ከዚያም በጨዋታቸው መሃል ሩት ስለ ቦዔዝ ደግነት ለኑኃሚን ነገረቻት። ኑኃሚንም በዚህ ተደስታ “በጎነቱን ለሕያዋንም ሆነ ለሙታን ማድረጉን ያልተወ እግዚአብሔር ይባርከው” አለች። (ሩት 2:20) ኑኃሚን፣ ቦዔዝን ደግነት እንዲያሳይ ያነሳሳው አገልጋዮቹ ለጋሶች እንዲሆኑ የሚያበረታታውና ሕዝቦቹ ለሚያሳዩት ደግነት ወሮታ እንደሚከፍል ቃል የገባው ይሖዋ እንደሆነ ገብቷታል። *—ምሳሌ 19:17ን አንብብ።
8 ቦዔዝ፣ ሩት እየመጣች በእሱ እርሻ ውስጥ እንድትቃርም እንዲሁም አጫጆቹ እንዳይተናኮሏት የቤተሰቡ አባላት ከሆኑት ወጣት ሴቶች አጠገብ እንዳትርቅ የሰጣትን ምክር እንድትከተል በመንገር ኑኃሚን ሩትን አበረታታቻት። ሩትም የተሰጣትን ምክር ተግባራዊ አድርጋለች። በተጨማሪም ሩት ‘ከአማቷ ጋር መኖሯን’ ቀጥላለች። (ሩት 2:22, 23) ይህ ጥቅስ የሩት መለያ የሆነውን ባሕርይ ማለትም ጽኑ ፍቅርን ጎላ አድርጎ ይገልጻል። የእሷ ምሳሌነት ‘የቤተሰባችንን አባላት በታማኝነት በመደገፍና አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ከጎናቸው በመሆን ለቤተሰብ ዝግጅት አክብሮት እንዳለን እያሳየን ነው?’ በማለት ራሳችንን እንድንጠይቅ ያነሳሳናል። ይሖዋ የምናሳየውን ጽኑ ፍቅር ምንጊዜም ይመለከታል።
ሩትና ኑኃሚን የተዉት ምሳሌ ለቤተሰባችን አድናቆት ሊኖረን እንደሚገባ ያሳስበናል
9. ከሩትና ከኑኃሚን ስለ ቤተሰብ ምን መማር እንችላለን?
9 ኑኃሚንና ሩት ቤተሰብ ተብለው መጠራት ይችላሉ? አንዳንዶች ቤተሰብ የሚባለው ባልን፣ ሚስትን፣ ልጆችን፣ አያቶችንና የመሳሰሉትን ያቀፈ ከሆነ ብቻ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ኑኃሚንና ሩት የተዉት ምሳሌ እንደሚያሳየው የይሖዋ አገልጋዮች ልባቸውን መክፈትና ጥቂት አባላት ባሉት ቤተሰብ ውስጥም እንኳ መተሳሰብ፣ ደግነትና ፍቅር እንዲሰፍን ማድረግ ይችላሉ። አንተስ ለቤተሰብህ አድናቆት አለህ? ኢየሱስ፣ ክርስቲያን ጉባኤ ቤተሰብ ለሌላቸውም እንኳ እንደ ቤተሰብ ሊሆንላቸው እንደሚችል ለተከታዮቹ ነግሯቸዋል።—ማር. 10:29, 30
“የመቤዠት ግዴታ ካለባቸው ዘመዶቻችን አንዱ እርሱ ነው”
10. ኑኃሚን ሩትን በምን ነገር ልትረዳት ትፈልግ ነበር?
10 ሩት የገብስ አዝመራ ከሚሰበሰብበት ከሚያዝያ ወር አንስቶ የስንዴ አዝመራ እስከሚደርስበት እስከ ሰኔ ድረስ በቦዔዝ እርሻ ላይ መቃረሟን ቀጠለች። ሳምንታት እያለፉ ሲሄዱ ኑኃሚን ለምትወዳት ምራቷ ምን ልታደርግላት እንደምትችል ማሰቧ አልቀረም። በሞዓብ እያሉ ኑኃሚን ለሩት ፈጽሞ ሌላ ባል ልታገኝላት እንደማትችል ተሰምቷት ነበር። (ሩት 1:11-13) አሁን ግን ሌላ አማራጭ እንዳለ ማሰብ ጀምራለች። ኑኃሚን ወደ ሩት ቀርባ “ልጄ ሆይ፤ የሚመችሽን ቤት እንድፈልግልሽ አይገባኝምን?” አለቻት። (ሩት 3:1) በዚያ ዘመን ወላጆች ለልጆቻቸው የትዳር ጓደኛ መፈለጋቸው የተለመደ ሲሆን ሩት ደግሞ ለኑኃሚን እንደ ልጇ ነበረች። በመሆኑም ኑኃሚን ሩት ‘የሚመቻት’ ወይም እረፍት የምታገኝበት ስፍራ እንዲኖራት ትፈልግ ነበር፤ ኑኃሚን ይህን ስትል ባል ማግባትና ኑሮ መመሥረት ሊያስገኝ የሚችለውን ጥበቃና የደህንነት ስሜት መግለጿ ነበር። ይሁን እንጂ ኑኃሚን ምን ልታደርግ ትችላለች?
11, 12. (ሀ) ኑኃሚን፣ ቦዔዝ “የመቤዠት ግዴታ” እንዳለበት ስትገልጽ በአምላክ ሕግ ውስጥ የተካተተውን የትኛውን ፍቅራዊ ዝግጅት መጥቀሷ ነው? (ለ) ሩት አማቷ ለለገሰቻት ምክር ምን ምላሽ ሰጠች?
11 ሩት ስለ ቦዔዝ ለኑኃሚን መጀመሪያ ስትነግራት ኑኃሚን “ሰውየው እኮ የሥጋ ዘመዳችን ነው፤ የመቤዠት ግዴታ ካለባቸው ዘመዶቻችን አንዱ እርሱ ነው” ብላት ነበር። (ሩት 2:20) ኑኃሚን ምን ማለቷ ነበር? አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ፣ በድህነትም ሆነ የቤተሰብ አባልን በሞት በማጣት የተነሳ ችግር ላይ የወደቁ ቤተሰቦችን የሚጠቅም ፍቅራዊ ዝግጅት ይዟል። አንዲት ሴት፣ ልጅ ሳትወልድ ባሏ ቢሞት ሐዘኗ የከፋ ይሆናል፤ ምክንያቱም ባሏ ዘር ሳይተካ ስለሞተ ወደፊት በስሙ የሚጠራ ዘር አይኖረውም። ይሁን እንጂ አምላክ ያወጣው ሕግ ይህች ሴት የባሏን ወንድም አግብታ የሟቹን ስም የሚያስጠራና የቤተሰቡን ንብረት የሚወርስ ልጅ እንድትወልድ ይፈቅድ ነበር። *—ዘዳ. 25:5-7
12 ኑኃሚን ከዚህ ጋር በተያያዘ ምን ለማድረግ እንዳቀደች ለሩት ነገረቻት። ወጣቷ ሩት፣ አማቷ ይህን ሐሳብ ስትናገር በመገረም ዓይኗ ፈጦ ስታዳምጣት በዓይነ ሕሊናችን መመልከት እንችላለን። ሩት ለእስራኤላውያን ሕግ ገና አዲስ ናት፤ ብዙዎቹ ልማዶችም ለእሷ እንግዳ ነበሩ። እንደዚያም ሆኖ ኑኃሚንን በጣም ታከብራት ስለነበር የነገረቻትን እያንዳንዱን ነገር በጥንቃቄ አዳመጠች። ኑኃሚን እንድታደርግ የጠየቀቻት ነገር ግራ የሚያጋባ፣ የሚያሳፍር አልፎ ተርፎም ለውርደት ሊዳርግ የሚችል ቢመስልም ሩት እንደተባለችው ለማድረግ ተስማማች። “ያልሽውን ሁሉ አደርጋለሁ” በማለት በትሕትና መለሰች።—ሩት 3:5
13. በዕድሜ የገፉ ሰዎች የሚሰጡንን ምክር በመቀበል ረገድ ከሩት ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን? (በተጨማሪም ኢዮብ 12:12ን ተመልከት።)
13 አንዳንድ ጊዜ ወጣቶች በዕድሜ የገፉና ተሞክሮ ያካበቱ ሰዎች የሚሰጧቸውን ምክር መስማት ይቸግራቸዋል። ወጣቶች በዕድሜ የገፉ ሰዎች እነሱ እያጋጠሟቸው ያሉትን ተፈታታኝ ሁኔታዎችና ችግሮች ሊረዱላቸው እንደማይችሉ ይሰማቸው ይሆናል። ሩት በትሕትና ረገድ የተወችው ምሳሌ ግን የሚወዱንና ለእኛ የሚያስቡልን በዕድሜ የገፉ ሰዎች የሚሰጡንን ጥበብ ያዘለ ምክር መስማት በእጅጉ እንደሚክስ ያሳያል። (መዝሙር 71:17, 18ን አንብብ።) ይሁን እንጂ ኑኃሚን ለሩት የሰጠቻት ምክር ምን ነበር? ደግሞስ ሩት ምክሩን በመቀበሏ ተክሳለች?
ሩት በአውድማው ላይ
14. አውድማ ምንድን ነው? ለምንስ ያገለግላል?
14 በዚያን ዕለት ምሽት ሩት ወደ አውድማው አመራች፤ አውድማ ገበሬዎች እህላቸውን የሚወቁበትና የሚያዘሩበት በደንብ ተጠቅጥቆ የተዘጋጀና የተስተካከለ መሬት ነው። ብዙውን ጊዜ ለአውድማነት የሚመረጠው ቦታ የተራራ ግርጌ ወይም ጉብታ ሲሆን ይህም የሚሆነው በእነዚህ አካባቢዎች አመሻሹ ላይ ነፋስ እንደ ልብ ስለሚነፍስ ነው። ገበሬዎቹ ምርቱን ከገለባውና ከእብቁ ለመለየት ሲሉ በመንሽ ወይም በላይዳ ያዘሩታል፤ እህሉ ክብደት ስላለው አውድማው ላይ ሲቀር እብቁን ግን ነፋስ ይወስደዋል።
15, 16. (ሀ) ቦዔዝ ምሽት ላይ ሥራውን ካጠናቀቀ በኋላ በአውድማው ላይ የነበረውን ሁኔታ ግለጽ። (ለ) ቦዔዝ፣ ሩት እግሩ ሥር መተኛቷን ያወቀው እንዴት ነበር?
15 ሩት ሠራተኞቹ ሥራቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ ተደብቃ ሁኔታውን ስትከታተል ቆየች። ቦዔዝ ሠራተኞቹ እህሉን እያዘሩ ምርቱን ከገለባው በመለየት አንድ ቦታ ላይ ሲቆልሉ በትኩረት ይከታተላል። ቦዔዝ ራቱን በደንብ ከበላ በኋላ በተቆለለው እህል አጠገብ ተኛ። በወቅቱ አውድማ ላይ ማደር የተለመደ ነገር ነበር፤ ይህም የሚደረገው ብዙ ጉልበት የፈሰሰበትን ምርት ከሌቦችና ከዘራፊዎች ለመጠበቅ ተብሎ ሳይሆን አይቀርም። ሩት፣ ቦዔዝ መተኛቱን ስታይ ኑኃሚን የነገረቻትን ነገር ተግባራዊ የምታደርግበት ሰዓት እንደደረሰ ተገነዘበች።
16 ሩት ከፍርሃት የተነሳ ልቧ በኃይል እየመታ ቀስ ብላ ወደ ቦዔዝ ተጠጋች። ሰውየው ጭልጥ ያለ እንቅልፍ እንደወሰደው ከሁኔታው ማስተዋል ችላለች። በመሆኑም ልክ ኑኃሚን እንደነገረቻት ወደ እሱ ሄዳ እግሩን ከገለጠች በኋላ እዚያው ጋደም አለች። ከዚያም የሚሆነውን ትጠብቅ ጀመር። ጊዜው ነጎደ። እነዚያ ሰዓታት ለሩት የዓመታት ያህል ረዝመውባት መሆን አለበት። በመጨረሻም እኩለ ሌሊት አካባቢ ሩት 3:8
ቦዔዝ መገላበጥ ጀመረ። ከዚያም ቅዝቃዜ ስለተሰማው ሳይሆን አይቀርም እግሩን ለማልበስ ቀና አለ። በዚህ ጊዜ እግሩ ሥር የተኛ ሰው እንዳለ አስተዋለ። ዘገባው “አንዲት ሴት እግርጌው ተኝታ አገኘ!” ይላል።—17. ሩት የፈጸመችው ነገር ተገቢ እንዳልሆነ አድርገው የሚያስቡ ሰዎች የትኞቹን ሁለት ግልጽ እውነታዎች ዘንግተዋል?
17 ቦዔዝ “አንቺ ማነሽ?” ሲል ጠየቃት። ሩት በፍርሃት ድምፅዋ እየተንቀጠቀጠ ሳይሆን አይቀርም “እኔ አገልጋይህ ሩት ነኝ፤ መቤዠት የሚገባህ ቅርብ የሥጋ ዘመድ አንተ ነህና ልብስህን ጣል አድርግብኝ” ብላ መለሰችለት። (ሩት 3:9) በዘመናችን ያሉ አንዳንድ ተንታኞች የሩት ድርጊትና ንግግር በተዘዋዋሪ የቀረበ የፆታ ጥያቄ እንደሆነ አድርገው ለማቅረብ ቢጥሩም እነዚህ ግለሰቦች የዘነጓቸው ሁለት ግልጽ እውነታዎች አሉ። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሩት ያደረገችው ነገር በወቅቱ በነበረው ልማድ ላይ የተመሠረተ ሲሆን እኛ ደግሞ በዚያ ዘመን ስለነበሩት አብዛኞቹ ልማዶች ያለን ግንዛቤ ውስን ነው። ስለዚህ አድራጎቷን በዛሬው ጊዜ ካለው የዘቀጠ የሥነ ምግባር መሥፈርት አንጻር መመዘን ስህተት ይሆናል። በሁለተኛ ደረጃ፣ ቦዔዝ የሰጠው ምላሽ የሩትን ተግባር የሚያስመሰግን እንጂ ከሥነ ምግባር አንጻር የሚያስነቅፍ እንደሆነ አድርጎ እንዳልተመለከተው በግልጽ የሚያሳይ ነው።
18. ቦዔዝ ሩትን የሚያጽናና ምን ነገር ተናገረ? ቦዔዝ ‘ከዚህ በፊት ያደረግሽው’ እና “ያሁኑ በጎነትሽ” በማለት ሲናገር ምን መጥቀሱ ነበር?
18 ቦዔዝ፣ ሩትን ያናገራት በደግነትና በሚያጽናና መንገድ እንደነበር ጥርጥር የለውም። እንዲህ አላት፦ “ልጄ ሆይ፤ እግዚአብሔር ይባርክሽ፤ ከዚህ በፊት ካደረግሽው ይልቅ ያሁኑ በጎነትሽ ይበልጣል፤ ባለጠጋም ሆነ ድኻ፣ ወጣት ወንድ ፈልገሽ አልሄድሽምና።” (ሩት 3:10) ቦዔዝ ‘ከዚህ በፊት ያደረግሽው’ ሲል ሩት፣ ኑኃሚንን ተከትላ ወደ እስራኤል በመምጣትና አማቷን በመንከባከብ ያሳየችውን ጽኑ ፍቅር መግለጹ ነው። “ያሁኑ በጎነትሽ” ያለው ደግሞ በዚያ ምሽት ያደረገችውን ነገር ለመጥቀስ ነው። ቦዔዝ እንደ ሩት ያለች ወጣት ሀብታምም ይሁን ድሃ የፈለገችውን ወጣት መርጣ ማግባት ትችል እንደነበር ተረድቷል። ሩት ግን የሟቹ የኑኃሚን ባል የዘር ሐረግ እንዲቀጥል በማድረግ ለኑኃሚን ብቻ ሳይሆን ለኑኃሚን ባል ጭምር መልካም ማድረግ ፈልጋ ነበር። ቦዔዝ፣ ይህች ወጣት በፈጸመችው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ድርጊት ልቡ የተነካው ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም።
19, 20. (ሀ) ቦዔዝ ሩትን ወዲያውኑ ያላገባት ለምንድን ነው? (ለ) ቦዔዝ ለሩት ደግነት ያሳያት እንዲሁም ለስሜቷም ሆነ ለስሟ እንደሚጠነቀቅ ያሳየው እንዴት ነው?
19 ቦዔዝ በመቀጠል እንዲህ አላት፦ “አሁንም ልጄ ሆይ፤ አትፍሪ፤ የምትጠይቂውን ሁሉ አደርግልሻለሁ፤ አንቺ ምግባረ መልካም ሴት መሆንሽንም የአገሬ ሰው ሁሉ ያውቀዋል።” (ሩት 3:11) ቦዔዝ፣ ሩትን የማግባት አጋጣሚ በማግኘቱ ደስ ብሎታል፤ ምናልባትም እሷን እንዲቤዣት ጥያቄ ሊቀርብለት እንደሚችል በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ጠብቆ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ቦዔዝ ጻድቅ ሰው ስለነበር ስለ ራሱ ፍላጎት ብቻ አላሰበም። በመሆኑም ከእሱ ይልቅ ለሟቹ የኑኃሚን ባል ቤተሰብ ይበልጥ ቅርብ የሆነ የመቤዠት ግዴታ ያለበት ሰው እንዳለ ለሩት ገለጸላት። ስለዚህ ቦዔዝ መጀመሪያ ይህን ሰው አግኝቶ እሷን ለማግባት ፈቃደኛ መሆን አለመሆኑን መጠየቅ ይኖርበታል።
ሩት ለሌሎች ደግነትና አክብሮት በማሳየቷ መልካም ስም አትርፋለች
20 ቦዔዝ፣ ሩትን እስኪነጋጋ ድረስ እዚያው እንድትተኛ ነገራት፤ ከዚያም ማንም ሰው ሳያያት ተነስታ ወደ ቤቷ መሄድ ትችላለች። ቦዔዝ የእሷም ሆነ የራሱ መልካም ስም እንዲጎድፍ አልፈለገም ነበር፤ ምክንያቱም ሰዎች ሩትን ቢያዩአት የሥነ ምግባር ብልግና እንደተፈጸመ አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ። ሩት ላቀረበችው ልመና ቦዔዝ በደግነት መልስ ስለሰጣት ጭንቀቷ ቀለል ብሎላት ተመልሳ በስተ ግርጌው ተኛች። ከዚያም ገና በደንብ ሳይነጋ ከእንቅልፏ ተነሳች። ቦዔዝም የደረበችውን ልብስ እንድትዘረጋው ከጠየቃት በኋላ ገብስ ሰፍሮ ሰጣት፤ እሷም የተሰጣትን እህል ተሸክማ ወደ ቤተልሔም ተመለሰች።—ሩት 3:13-15ን አንብብ።
21. ሩት መልካም ስም እንድታተርፍ አስተዋጽኦ ያደረገው ምንድን ነው? እኛስ የእሷን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
21 ሩት፣ በሰው ሁሉ ዘንድ “ምግባረ መልካም ሴት” በመሆኗ እንደምትታወቅ ቦዔዝ የነገራትን መለስ ብላ ስታስብ ምን ያህል ተደስታ ይሆን! እንዲህ ያለ መልካም ስም እንድታተርፍ አስተዋጽኦ ያደረገው ይሖዋን ለማወቅና እሱን ለማገልገል ያላት ከፍተኛ ፍላጎት እንደሆነ ጥርጥር የለውም። በተጨማሪም ለእሷ ፈጽሞ እንግዳ የሆኑ ልማዶችንና ባሕሎችን ለመቀበል ፈቃደኛ በመሆን ለኑኃሚንም ሆነ ለሕዝቧ ታላቅ ደግነትና አሳቢነት አሳይታለች። እኛም ሩትን በእምነቷ የምንመስላት ከሆነ ለሰዎች አሳቢነት ለማሳየት እንዲሁም ባሕላቸውንና ልማዳቸውን በጥልቅ ለማክበር እንጥራለን። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ እኛም ልክ እንደ ሩት መልካም ስም እናተርፋለን።
ለሩት የሚሆን የእረፍት ቦታ
22, 23. (ሀ) ቦዔዝ ለሩት የሰጣት ስጦታ ምን ትርጉም ሊኖረው ይችላል? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።) (ለ) ኑኃሚን ሩትን ምን እንድታደርግ ነገረቻት?
22 ሩት ቤት ስትደርስ ኑኃሚን “ልጄ፣ አንቺ ማነሽ?” አለቻት። ምናልባትም ኑኃሚን እንዲህ ብላ የጠየቀቻት በደንብ ስላልነጋ ማንነቷን መለየት አቅቷት ሊሆን ይችላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ኑኃሚን፣ ሩት እንደ ቀድሞዋ ብቸኛ መበለት ናት ወይስ የሚያገባት ሰው አግኝታለች የሚለውን ማወቅ ፈልጋ ይሆናል። ከዚያም ሩት ከቦዔዝ ጋር የተነጋገሩትን በሙሉ ለአማቷ ነገረቻት። በተጨማሪም ቦዔዝ ለኑኃሚን የላከላትን ገብስ ሰጠቻት። *—ሩት 3:16, 17 NW
23 ብልህ የሆነችው ኑኃሚን፣ ሩትን በዚያ ቀን ለመቃረም ወደ እርሻው በመሄድ ፈንታ ቤት እንድትውል መከረቻት። እንዲሁም “ጕዳዩ ዛሬውኑ እልባት ካላገኘ ሰውየው አያርፍም” የሚል ማረጋገጫ ሰጠቻት።—24, 25. (ሀ) ቦዔዝ ቅንና ራስ ወዳድ ያልሆነ ሰው መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ሩት የተባረከችው እንዴት ነው?
24 ኑኃሚን ስለ ቦዔዝ የተናገረችው ነገር ትክክል ነበር። ቦዔዝ፣ አብዛኛውን ጊዜ የከተማዋ ሽማግሌዎች ወደሚሰባሰቡበት ወደ ከተማዋ በር ሄዶ የቅርብ ዘመድ የሆነው ሰው በዚያ ሲያልፍ ለማግኘት ይጠባበቅ ጀመር። ከዚያም ቦዔዝ፣ ሰውየው ሩትን በማግባት ቤተሰቡን የመቤዠት መብት እንዳለው በምሥክሮች ፊት ነገረው። ይሁን እንጂ ሰውየው እንዲህ ማድረጉ የራሱን ርስት አደጋ ላይ ሊጥልበት እንደሚችል በመግለጽ ለመቤዠት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ተናገረ። ከዚያም ቦዔዝ፣ የሟቹን የኑኃሚንን ባል የአቤሜሌክን ርስት በመግዛትና የአቤሜሌክ ልጅ የመሐሎን ሚስት የነበረችውን ሩትን በማግባት ቤተሰቡን እንደሚቤዥ በከተማዋ በር ባሉት ምሥክሮች ፊት ተናገረ። ቦዔዝ እንዲህ በማድረግ “የሟቹን ስም በርስቱ ላይ ለማስጠራት” ፈቃደኛ እንደሆነ ገለጸ። (ሩት 4:1-10) ቦዔዝ በእርግጥም ቅንና ራስ ወዳድ ያልሆነ ሰው ነበር።
25 ቦዔዝ ሩትን አገባት። ዘገባው ከዚያ በኋላ ስለሆነው ነገር ሲገልጽ “እግዚአብሔር እንድትፀንስ አደረጋት፤ ወንድ ልጅም ወለደች” ይላል። የቤተልሔም ሴቶች ኑኃሚንን የመረቋት ሲሆን ሩትንም ለኑኃሚን ከሰባት ወንዶች ልጆች ይልቅ የተሻለች ሆና በመገኘቷ አሞገሷት። ከጊዜ በኋላም የሩት ልጅ የንጉሥ ዳዊት አያት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሩት 4:11-22) ዳዊት ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት ነው።—ማቴ. 1:1 *
26. ሩትና ኑኃሚን የተዉት ምሳሌ ምን ነገር ያስገነዝበናል?
26 ሕፃኑን እንደ ራሷ ልጅ አድርጋ እንዳሳደገችው እንደ ኑኃሚን ሁሉ ሩትም ተባርካለች። የእነዚህ ሁለት ሴቶች ሕይወት፣ ይሖዋ ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ለማሟላት ደፋ ቀና ለሚሉና ከተመረጡ ሕዝቦቹ ጋር ሆነው በታማኝነት ለሚያገለግሉ ሁሉ ትኩረት እንደሚሰጥ የሚያሳይ ሕያው ማስረጃ ነው። ይሖዋ እንደ ቦዔዝ፣ ኑኃሚንና ሩት ላሉት ታማኝ ሕዝቦቹ ወሮታ ከመክፈል ፈጽሞ ወደኋላ አይልም።
^ አን.7 ኑኃሚን እንደገለጸችው ይሖዋ ደግነት የሚያሳየው በሕይወት ላሉት ብቻ ሳይሆን ለሞቱትም ጭምር ነው። ኑኃሚን ባሏንና ሁለቱን ወንዶች ልጆቿን በሞት አጥታለች። ሩትም ባሏን በሞት ተነጥቃለች። እነዚያ ሦስት ወንዶች በሁለቱ ሴቶች ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ እንደነበራቸው ጥርጥር የለውም። ለሩትና ለኑኃሚን የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ደግነት እነዚህ ሴቶች ጥሩ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ይፈልጉ ለነበሩት ለእነዚያ ወንዶች እንደተደረገ የሚቆጠር ነው።
^ አን.11 ከውርስ ጋር በተያያዘ እንደሚደረገው ሁሉ በዚህ ጊዜም ባሏ የሞተባትን ሴት የማግባት መብት በመጀመሪያ ለሟቹ ወንድሞች ይሰጣል፤ እነሱ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ ይህ መብት የቅርብ ዘመዱ ለሆነ ወንድ ይሰጥ ነበር።—ዘኍ. 27:5-11
^ አን.22 ቦዔዝ ለሩት ስድስት መስፈሪያ (መለኪያው አልተገለጸም) ገብስ መስጠቱ፣ ከስድስት የሥራ ቀናት በኋላ የሰንበት እረፍት እንደሚኖር ሁሉ ሩትም በመበለትነት ያሳለፈችው የልፋት ዘመን አብቅቶ ባል ማግባትና ኑሮ መመሥረት የሚያስገኘውን እረፍት የምታጣጥምበት ጊዜ እንደቀረበ ለመጠቆም ብሎ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ምናልባትም በላይዳ እየዛቀ የሰጣት ገብስ ስድስት መስፈሪያ ብቻ የሆነው ሩት ከዚያ በላይ ልትሸከም ስለማትችል ሊሆን ይችላል።