5 አብርሃም
በከባዱ ተፈተነ
አብርሃም ጉዞ ጀምሯል፤ ሂድ ወደተባለበት ቦታ እያዘገመ ነው። ጉዞው ጥቂት ቀናት ቢወስድ ነው፤ ባሳለፈው ረጅም ሕይወት ግን ይህን ያህል የከበደው ጉዞ የለም።
ይሖዋ እንዲያደርግ የጠየቀውን ነገር እያወጣና እያወረደ ነው። “እባክህ ልጅህን፣ በጣም የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያ ምድር ሂድ፤ በዚያም እኔ በማሳይህ በአንዱ ተራራ ላይ የሚቃጠል መባ አድርገህ አቅርበው” ብሎታል። አብርሃም ለይስሐቅ ምን ያህል እንደሚሳሳ ይሖዋ ያውቃል። ታዲያ እንዴት እንዲህ ያለ ነገር ይጠይቀዋል? አብርሃምስ ይህን ትእዛዝ ለመፈጸም የሚያስችል እምነትና ድፍረት የሚያገኘው ከየት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ አብርሃምን ‘እምነት ላላቸው ሁሉ አባት’ በማለት ይጠራዋል። (ሮም 4:11) ይህን ጉዞ ከመጀመሩ ከረጅም ጊዜ በፊትም አብርሃም አስደናቂ እምነት አሳይቷል፤ ይሖዋም እምነቱ እንዲጠናከር ረድቶታል። ለምሳሌ ያህል፣ ከብዙ ዓመታት በፊት አምላክ ክፉ የሆኑትን የሰዶምና የገሞራ ከተሞች እንደሚያጠፋ ለአብርሃም ነግሮት ነበር። ይህ አብርሃምን በጣም ረበሸው፤ በመሆኑም ጥሩውን ከመጥፎው ጋር ያጠፋ እንደሆነ ይሖዋን ጠየቀው። ይሖዋ፣ ጥቂት ጻድቃን ሰዎች ቢኖሩ እንኳ ከተሞቹን እንደሚምራቸው ለአብርሃም በትዕግሥት አስረድቶታል። (ዘፍ. 18:16-33) አብርሃም በዚህ ወቅት ያገኘውን ትምህርት ፈጽሞ አይረሳውም፤ ይሖዋ ፍትሐዊና መሐሪ ነው።
አብርሃም፣ ለልጁ የሚሳሳ አንድ አባት ፈጽሞ የማያስበውን ነገር እንዲያደርግ ይሖዋ ሲጠይቀው ለመታዘዝ ድፍረት ያገኘው እንዴት ነው?
ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ለአብርሃምና ለሣራ ተአምራዊ ስጦታ ሰጣቸው። ሣራ ወደ 90 አብርሃም ደግሞ ወደ 100 ዓመት እየተጠጉ ቢሆንም ይሖዋ በተአምር ልጅ የመውለድ ችሎታ እንዲኖራቸው አድርጓል፤ ይስሐቅን ሰጥቷቸዋል! አብርሃም ለይሖዋ የሚሳነው ነገር እንደሌለ ተምሯል፤ ‘የሞተ ነው’ በተባለ ነገር ላይ እንኳ ሕይወት ሊዘራበት እንደሚችል ተረድቷል። (ሮም 4:18, 19) አብርሃም ይህኛውን ቁም ነገርም ቢሆን ፈጽሞ አይረሳውም።
አሁን ይህ ከሆነ 25 ዓመታት አልፈዋል፤ አብርሃም ወደ ሞሪያ ሲጓዝ፣ በሕይወቱ ያገኛቸውን እነዚህን ትምህርቶች መልሶ መላልሶ እያሰበ መሆን አለበት። አንድ መደምደሚያ ላይ ደረሰ፦ ይስሐቅ ቢሞት እንኳ ይሖዋ ሊያስነሳው ይችላል፤ ደግሞም ሊያስነሳው ይፈልጋል! (ዕብ. 11:19) ስለዚህ አብርሃም በዚህ ተስፋ ራሱን አደፋፍሮ ጉዞውን ቀጠለ።
አብርሃም ይሖዋ የመረጠውን ቦታ ከርቀት ሲያይ፣ እሱና ይስሐቅ ተራራው ላይ ወጥተው መሥዋዕት አቅርበው እስኪመለሱ እዚያው እንዲቆዩአቸው ለአገልጋዮቹ ነገራቸው። የአብርሃም አነጋገር እሱም ሆነ ይስሐቅ እንደሚመለሱ እርግጠኛ እንደነበረ ያሳያል። አብርሃምና ይስሐቅ ተራራው ላይ ወጥተው ብቻቸውን ሲሆኑ አምላክ ያዘዘውን የሚፈጽምበት ሰዓት ደረሰ። ይስሐቅን አስሮ መሠዊያው ላይ አጋደመው፤ ይስሐቅም አረጋዊው አባቱ ይህን ሲያደርግ እሺ ብሎ ታዘዘ። አብርሃም ቢላውን አንስቶ ፈጽሞ የማይታሰበውን ሊያደርግ ሲል አንድ መልአክ ጠራው፤ “በልጁ ላይ እጅህን አታሳርፍበት” አለው።
ከዚያም አምላክ አብርሃምን በእምነቱና በታዛዥነቱ አደነቀው። እንደሚባርከውና ዘሩን እንደሚያበዛ የገባውን ቃል ደገመለት፤ ባሳየው ታዛዥነት የተነሳ “የምድር ብሔራት ሁሉ” ብዙ በረከት እንደሚያገኙም ነገረው።
ይሖዋ ለአብርሃም የገባው ቃል አሁንም እየተፈጸመ ነው። ገና ለዘላለም የሚዘልቁ በረከቶች ያስገኛል። ይሖዋ፣ አብርሃምን እንዲያደርግ በጠየቀው ነገር አማካኝነት ሌላም ያሳወቀን ነገር አለ። እሱ ራሱ ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆችን በሙሉ ለማዳን ሲል በራሱ ላይ እንዲደርስ የፈቀደውን ነገር አስገንዝቦናል። አብርሃም የሚወደውን ልጁን መሥዋዕት ለማድረግ እንዳልሳሳ ሁሉ ይሖዋም የሰውን ዘር ለመጥቀም ሲል አንድያ ልጁን ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኗል። (ዮሐ. 3:16) በመሆኑም አብርሃም ለእሱ እጅግ ውድ የሆነውን ነገር ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን ስናነብ የይሖዋን ፍቅር ጥልቀትም እንማራለን።
እኛም እንደ አብርሃም ይሖዋ ቀደም ሲል በተናገራቸውና ባደረጋቸው ነገሮች ላይ የምናሰላስል ከሆነ እምነታችን ያድጋል። እምነታችን ሲያድግ ደግሞ ድፍረታችን ይጨምራል። እርግጥ ነው፣ አምላክ አብርሃምን ያዘዘውን ነገር እንድናደርግ ይጠይቀናል ብለን አንጠብቅም። ከአብርሃም ወዲህ ማንንም እንዲህ እንዲያደርግ ጠይቆ አያውቅም። በእርግጠኝነት የምናውቀው አንድ ነገር ግን አለ፦ አምላክ የጠየቀን ነገር ምንም ይሁን ምን በእሱ ላይ እምነት ካለን ለመታዘዝ ድፍረት ይኖረናል። ታዛዥነታችን ደግሞ ከምንገምተው በላይ ብዙ በረከት ያስገኝልናል!
ታሪኩን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንብብ፦
ለውይይት፦
አብርሃም እነዚህ ክንውኖች በተፈጸሙበት ወቅት ድፍረት ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
ጠለቅ ብለህ መርምር
-
1. አብርሃም በእውን የነበረ ሰው መሆኑን የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ? (g 5/12 18 ሣጥን፤ it “አብርሃም” አን. 22-23-wcgr) ሀ
ሥዕል ሀ፦ በካርናክ፣ ግብፅ የተገኘ ግድግዳ ላይ የተቀረጸ ጽሑፍ “የአብራም እርሻ” ይላል
-
2. አብርሃም ስለ ይሖዋ አምላክ ያወቀው እንዴት ሊሆን ይችላል? (ia 26 አን. 4-5)
-
3. የአብርሃም አምልኮ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው ለምንድን ነው? (rr 20 አን. 18)
-
4. በዘፍጥረት 22:17 ላይ ይሖዋ ለአብርሃም የገባው ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ አንጻር ትክክለኛ መሆኑን የሚያረጋግጠው እንዴት ነው? (g88 4/8 25-wcgr) ለ
ሥዕል ለ
ሥዕል ለ
ምን እንደሚያስተምርህ አስብ
-
ተስፋ አብርሃምን ደፋር እንዲሆን የረዳው እንዴት ነው? እኛስ በተስፋችን ላይ ማተኮራችን ደፋሮች እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው? ሐ
ሥዕል ሐ
-
የአብርሃምን ድፍረት በመኮረጅ በሚከተሉት አቅጣጫዎች መሥዋዕት ማቅረብ የምንችለው እንዴት ነው?
-
አብርሃም በዚህ ታሪክ ላይ ያሳየውን ድፍረት በሕይወትህ ውስጥ በየትኞቹ ሌሎች መንገዶች መኮረጅ ትችላለህ?
በትልቁ ነገር ላይ አሰላስል
-
ይህ ታሪክ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል?
-
ይህ ታሪክ ከይሖዋ ዓላማ ጋር ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?
-
አብርሃምና ይስሐቅ ከሞት ሲነሱ ምን ልጠይቃቸው እፈልጋለሁ?
እውቀትህን አስፋ
በዚህ ታሪክ ላይ ያሉት ክንውኖች ሕያው በሆነ መንገድ የቀረቡበትን ትረካ ተመልከት።
አብርሃም የይሖዋ የቅርብ ወዳጅ የሆነው እንዴት ነው? አንተስ ከእሱ ጋር ያለህን ወዳጅነት ማጠናከር የምትችለው እንዴት ነው?

