በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንተ የምታምነው በምንድን ነው?

አንተ የምታምነው በምንድን ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ ቃል በቃል መቀበል አለብን የሚሉ ብዙ ሰዎች፣ ምድርና በምድር ላይ ያሉ ነገሮች በሙሉ የተፈጠሩት የ24 ሰዓት ርዝመት ባላቸው ስድስት ቀናት ውስጥ እንደሆነና ይህም የተከናወነው ከጥቂት ሺህ ዓመታት በፊት መሆኑን ያምናሉ። አምላክ የለሽ የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ አምላክ የሚባል ነገር እንደሌለ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በተረት የተሞላ መጽሐፍ እንደሆነ እንዲሁም ሕይወት ያለው ነገር በሙሉ እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ እንደሆነ ሊያሳምኑህ ይፈልጋሉ።

አብዛኞቹ ሰዎች እነዚህን ተቃራኒ ሐሳቦች ሙሉ በሙሉ ባይቀበሉም በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸው አመለካከት በእነዚህ ሁለት ጎራዎች መካከል ነው። ይህን ብሮሹር ማንበብህ በራሱ ከእነዚህ ሰዎች አንዱ መሆንህን ያመለክታል። በአምላክ የምታምን እንዲሁም ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ያለህ ሰው ልትሆን ትችላለህ። በሌላ በኩል ደግሞ ሕይወት በፍጥረት እንደተገኘ የማያምኑ በሙያቸው አንቱ የተሰኙና ከፍተኛ ተደማጭነት ያላቸው የሳይንስ ሊቃውንት ለሚሰነዝሩት አስተያየት ትልቅ ግምት ትሰጥ ይሆናል። ወላጅ ከሆንክ ደግሞ ልጆችህ ስለ ዝግመተ ለውጥና ስለ ፍጥረት ቢጠይቁህ ምን ብለህ እንደምትመልስላቸው ግራ ይገባህ ይሆናል።

የዚህ ብሮሹር ዓላማ ምንድን ነው?

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ ቃል በቃል መከተል አለብን የሚሉትንም ሆነ በአምላክ ላለማመን የመረጡትን ሰዎች አመለካከት መተቸት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህ ብሮሹር የተዘጋጀው የምታምንባቸው አንዳንድ ነገሮች በተጨባጭ ማስረጃ የተደገፉ መሆን አለመሆናቸውን መለስ ብለህ እንድትገመግም ለመርዳት ታስቦ ነው። ብሮሹሩ ስለ ፍጥረት የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ፣ ምናልባትም ከዚህ ቀደም ባላሰብከው አቅጣጫ ያብራራል። ከዚህም በተጨማሪ ይህ ጽሑፍ ስለ ሕይወት አመጣጥ የምታምነው ነገር ትልቅ ለውጥ የሚያመጣው ለምን እንደሆነ ይገልጻል።

ፈጣሪ እንደሌለና መጽሐፍ ቅዱስ እምነት ሊጣልበት እንደማይችል የሚናገሩ ሰዎችን አመለካከት መቀበል ይሻልሃል? ወይስ የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ ራስህ መመርመርን ትመርጣለህ? የትኛውን ትምህርት ብታምን ያዋጣሃል? የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ወይስ የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ? (ዕብራውያን 11:1) ትክክለኛውን ትምህርት ለማወቅ ማስረጃዎቹን እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።