በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጀመሪያውን ንድፍ ያወጣው ማን ነው?

የመጀመሪያውን ንድፍ ያወጣው ማን ነው?

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሳይንስ ሊቃውንትና መሐንዲሶች ለዕፅዋትና ለእንስሳት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ከእነሱ ለመማር ጥረት እያደረጉ ነው። (ኢዮብ 12:7, 8) አዳዲስ ነገሮችን ለማምረትና ያሉትንም ለማሻሻል የተለያዩ ፍጥረታትን ንድፍ በማጥናት ለመኮረጅ የሚሞክሩ ሲሆን ይህ መስክ ባዮሚሜቲክስ ይባላል። የሚከተሉትን ምሳሌዎች በምትመለከትበት ጊዜ ‘እንዲህ ላለው ንድፍ በእርግጥ ሊመሰገን የሚገባው ማን ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ።

ከዓሣ ነባሪ መቅዘፊያ መማር

የአውሮፕላን ንድፍ አውጪዎች ሃምፕባክ ከሚባለው የዓሣ ነባሪ ዝርያ ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ? ብዙ ሊማሩ የሚችሉት ነገር ያለ ይመስላል። ለአካለ መጠን የደረሰ ሃምፕባክ ዓሣ ነባሪ ወደ 300 ኩንታል የሚያህል ክብደት ሲኖረው ይህም ሙሉ ጭነት ከጫነ ከባድ መኪና ጋር ይስተካከላል፤ ይህ ዓሣ ነባሪ ሰውነቱ በቀላሉ የማይተጣጠፍ ሲሆን የክንፍ ቅርጽ ያለው በጣም ትልቅ መቅዘፊያ አለው። አሥራ ሁለት ሜትር ርዝመት ያለው ይህ እንስሳ በባሕር ውስጥ ሲንቀሳቀስ በጣም ቀልጣፋ ነው።

ተመራማሪዎችን በተለይ ያስደነቃቸው ነገር እንደልቡ መተጣጠፍ የማይችለው ይህ እንስሳ በጣም ጠባብ በሆነ ቦታ መዞር መቻሉ ነበር። ተመራማሪዎቹ ሚስጥሩ ያለው በዓሣ ነባሪው መቅዘፊያ ቅርጽ ላይ እንደሆነ አውቀዋል። የመቅዘፊያው ፊተኛ ጠርዝ እንደ አውሮፕላን ክንፍ ልሙጥ ሳይሆን ወጣ ገባ ነው።

ዓሣ ነባሪው ውኃውን እየሰነጠቀ በፍጥነት በሚንቀሳቀስበት ጊዜ እነዚህ ወጣ ገባዎች፣ ዓሣ ነባሪውን ወደ ላይ በመግፋት እንዲንሳፈፍ የሚያደርገው ግፊት እንዲጨምር ያደርጋሉ፤ እንዲሁም ዓሣ ነባሪውን ወደኋላ የሚጎትተውን የውኃ ግፊት በመቀነስ ወደፊት የመወንጨፍ ኃይል ይጨምሩለታል። እንዴት? ናቹራል ሂስትሪ የተባለው መጽሔት እንደገለጸው ዓሣ ነባሪው ሽቅብ በሚወጣበት ጊዜም እንኳ ወጣ ገባዎቹ ውኃው ክብ ቅርጽ በመሥራት ከመቅዘፊያው በላይ ሥርዓት ባለው መንገድ በፍጥነት እንዲያልፍ ያስችላሉ።10

በተፈጥሮ ውስጥ ለሚታየው ንድፍ የፈጠራ ባለቤትነት መብት ሊሰጠው የሚገባው ማን ነው?

ይህ ግኝት እንዴት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል? በዚህ ዲዛይን የተሠሩ የአውሮፕላን ክንፎች፣ የሚኖሯቸው የአየር ፍሰት አቅጣጫን ለማስቀየር የሚያገለግሉ ተንቀሳቃሽ የኋላ ጠርዞች (ዊንግ ፍላፕ) ወይም ሌሎች መሣሪያዎች ጥቂት ይሆናሉ። እንደነዚህ ያሉት የአውሮፕላን ክንፎች አደጋ የማስከተላቸው አጋጣሚ አነስተኛ ሲሆን ለመጠገንም ቀላል ይሆናሉ። የባዮሜካኒክስ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ጆን ሎንግ፣ በቅርቡ “እያንዳንዱ አውሮፕላን የሃምፕባክ ዓሣ ነባሪ መቅዘፊያ ዓይነት ክንፍ ተሠርቶለት ማየታችን አይቀርም” ብለዋል።11

ሲገል የተባለውን ወፍ ክንፍ መኮረጅ

የአውሮፕላን ክንፍ ቀድሞውንም ቢሆን የተሠራው የአእዋፍን ክንፍ በመኮረጅ ነው። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሐንዲሶች የወፎችን ክንፍ በመኮረጅ ረገድ ትልቅ እመርታ አሳይተዋል። ኒው ሳይንቲስት መጽሔት እንደዘገበው “በፍሎሪዳ ዩኒቨርስቲ የሚሠሩ ተመራማሪዎች እንደ ሲገል አንድ ቦታ ላይ ተንሳፍፎ መቆየት፣ ቁልቁል መወርወርና ሽቅብ መወንጨፍ የሚችል ያለ አብራሪ በርቀት መቆጣጠሪያ የሚንቀሳቀስ የሙከራ አውሮፕላን ሠርተዋል።”12

ሲገሎች የክንፎቻቸውን መገጣጠሚያዎች በማንቀሳቀስ በአየር ላይ አስደናቂ የሆነ ትርዒት ያሳያሉ። እንደልብ የሚተጣጠፈውን የሲገሎችን ክንፍ በመኮረጅ የተሠራው “[61 ሴንቲ ሜትር] ርዝመት ያለው አብራሪ አልባ የሙከራ አይሮፕላን፣ ክንፎቹን ለማንቀሳቀስ የሚያገለግሉትን የብረት ዘንጎች ለመቆጣጠር የሚያስችል አንድ ትንሽ ሞተር አለው” በማለት መጽሔቱ ዘግቧል። በተራቀቀ መንገድ የተሠሩት እነዚህ ክንፎች ትንሹ አውሮፕላን አንድ ቦታ ላይ ተንሳፍፎ እንዲቆይም ሆነ በትላልቅ ሕንፃዎች መካከል ቀጥ ብሎ ቁልቁል እንዲወርድ ያስችሉታል። በውትድርና መስክ የተሰማሩ አንዳንድ ሰዎች ወደተፈለገው አቅጣጫ በቀላሉ መታጠፍ የሚችለውን እንዲህ ያለ አውሮፕላን በትላልቅ ከተሞች ውስጥ ኬሚካላዊ ወይም ባዮሎጂያዊ የጦር መሣሪያዎችን አድኖ በመያዝ ረገድ ጥቅም ላይ ለማዋል ጓጉተዋል።

የሲገልን እግር መኮረጅ

ሲገል በረዶ ላይ ቢቆምም እንኳ ሰውነቱ አይቀዘቅዝም። ይህ ወፍ የሰውነቱን ሙቀት ጠብቆ የሚያቆየው እንዴት ነው? በተወሰነ መጠን ሚስጥሩ ያለው በቀዝቃዛ አካባቢዎች የሚኖሩ እንስሳት ባላቸው አስደናቂ ንድፍ ላይ ነው።

ሙቀት ይተላለፋል፤ የሰውነቱ ሙቀት እንደተጠበቀ ይቆያል። ቅዝቃዜው ከእግሮቹ አልፎ አይሄድም

ይህን አስደናቂ ንድፍ ለመረዳት ጎን ለጎን ተጠጋግተው አንድ ላይ የታሠሩ ሁለት የውኃ ቧንቧዎችን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በአንደኛው ቧንቧ ቀዝቃዛ ውኃ በሌላኛው ደግሞ ሙቅ ውኃ ያልፋል። ሙቁም ሆነ ቀዝቃዛው ውኃ በአንድ አቅጣጫ የሚሄዱ ከሆነ በትኩስ ውኃው ውስጥ ያለው ሙቀት ወደ ቀዝቃዛው ውኃ የሚተላለፈው በግማሽ ነው። ይሁን እንጂ ሙቁ ውኃና ቀዝቃዛው ውኃ በተቃራኒ አቅጣጫ የሚፈሱ ከሆነ ሙቀቱ ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል፣ ከሙቁ ውኃ ወደ ቀዝቃዛው ውኃ ይተላለፋል።

ሲገል በእግሮቹ ውስጥ የሚገኙት የደም ሥሮች የተጠጋጉ በመሆናቸው በረዶ ላይ በሚቆምበት ጊዜ ከሰውነቱ ወደ እግሩ የሚወርደው የሞቀ ደም ከወፉ እግር ወደ ሰውነቱ የሚመለሰውን ቀዝቃዛ ደም ያሞቀዋል። በዚህ መንገድ በወፉ ሰውነት ውስጥ ያለው ሙቀት እንደተጠበቀ የሚቆይ ሲሆን በእግሮቹ በኩል ሙቀት አይባክንም። የሜካኒካልና የአውሮፕላን መሐንዲስ የሆኑት አርተር ፍራስ የዚህ ወፍ እግር ንድፍ “በዓለም ላይ ካሉት አንድን ነገር ወደነበረበት የሙቀት መጠን እንደገና ለመመለስ የሚረዱ ሙቀት ማስተላለፊያ ዘዴዎች ሁሉ ይበልጥ ውጤታማ” መሆኑን ገልጸዋል።13 ይህ ንድፍ በጣም አስደናቂ በመሆኑ መሐንዲሶች ኮርጀውታል።

ለዚህ ሁሉ ሊመሰገን የሚገባው ማን ነው?

ቦክስፊሽ የሚባለውን ዓሣ ንድፍ በመኮረጅ የአየሩን ግፊት በቀላሉ ሰንጥቆ ማለፍ የሚችል አስተማማኝ መኪና ለመሥራት እየተሞከረ ነው

ብሔራዊ የበረራና የሕዋ አስተዳደር (NASA) እንደ ጊንጥ የሚራመድ ብዙ እግሮች ያሉት ሮቦት በመሥራት ላይ ነው፤ በፊንላንድ ያሉ መሐንዲሶች እንደ ትላልቅ ጉንዳኖች ከፊቱ የተጋረጡ እንቅፋቶችን ተራምዶ ማለፍ የሚችል ባለ ስድስት እግር ትራክተር ሠርተዋል። ሌሎች ተመራማሪዎች ደግሞ የጥድ ዝርያ የሆኑ ዛፎችን ዘር አቃፊ ፍሬዎች አሠራር በመኮረጅ ለየት ያለ ጨርቅ ሠርተዋል፤ የእነዚህ ዛፎች ዘር አቃፊ፣ አየሩ ሲሞቅ ዘሮቹ እንዲወጡ የሚከፈት ሲሆን አየሩ ሲቀዘቅዝ ደግሞ ይዘጋል። በዚህ መንገድ የተሠራው ጨርቅ እንደ ለባሹ የሰውነት ሙቀት ሊከፈቱና ሊከደኑ የሚችሉ ትናንሽ ነገሮች ስላሉት ግለሰቡ አየር እንዲያገኝ ወይም ሙቀቱ ተጠብቆ እንዲቆይ ያደርጋል። አንድ የመኪና አምራች ኩባንያ ቦክስፊሽ የሚባለውን የዓሣ ዝርያ ንድፍ በመኮረጅ የአየሩን ግፊት በቀላሉ ሰንጥቆ ማለፍ የሚችል መኪና በመሥራት ላይ ነው። አበሎኒ የተባለው የባሕር እንስሳ ራሱን የሚሸፍንበት ዛጎል አለው፤ አንዳንድ ተመራማሪዎች ዛጎሉ ያለውን ንዝረት ውጦ የማስቀረት ችሎታ በመቅዳት ይበልጥ ቀላልና ጠንካራ የሆነ የጥይት መከላከያ ሰደርያ ለመሥራት እየሞከሩ ነው።

ዶልፊን በድምፅ ሞገድ ተጠቅሞ የአንድን ነገር ርቀትና አቅጣጫ የማወቅ ችሎታው ሰው ከሠራው ተመሳሳይ መሣሪያ ይበልጣል

ከተፈጥሮ በጣም ብዙ ጠቃሚ ሐሳቦች በመገኘታቸው ምክንያት ተመራማሪዎች ሕይወት ካላቸው ነገሮች የተወሰዱ በሺዎች የሚቆጠሩ ንድፎችን መዝግቦ የሚይዝ የመረጃ ማዕከል አዘጋጅተዋል። ዚ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት እንደገለጸው ሳይንቲስቶች “ከንድፍ ጋር በተያያዘ ለሚገጥሟቸው ችግሮች ከተፈጥሮ መፍትሔ” ለማግኘት በዚህ የመረጃ ማዕከል ውስጥ ምርምር ማድረግ ይችላሉ። ተመራማሪዎች በዚህ የመረጃ ማዕከል ውስጥ የተካተቱት የተፈጥሮ ንድፎች፣ ባዮሎጂያዊ የፈጠራ ባለቤትነት (ባዮሎጂካል ፓተንት) እንዳላቸው ይገልጻሉ። በተለምዶ የፈጠራ ባለቤትነት መብት የሚያገኘው አንድን አዲስ ሐሳብ ወይም መሣሪያ በሕጋዊ መንገድ ያስመዘገበ ሰው ወይም ኩባንያ ነው። ዚ ኢኮኖሚስት ባዮሎጂያዊ የፈጠራ ባለቤትነት ስለሚመዘገብበት ስለዚህ የመረጃ ማዕከል ሲጽፍ “ተመራማሪዎች የባዮሚሜቲክስ ድንቅ ንድፎች ‘ባዮሎጂያዊ የፈጠራ ባለቤትነት’ እንዳላቸው ሲገልጹ በተዘዋዋሪ የንድፉ ባለቤት ተፈጥሮ እንደሆነ መግለጻቸው ነው” ብሏል።14

የሳይንስ ሊቃውንት የአበሎኒ ዛጎሎች ባላቸው ንዝረትን ውጦ የማስቀረት ችሎታ ላይ ምርምር እያደረጉ ነው

ታዲያ ተፈጥሮ እነዚህን ሁሉ ድንቅ ንድፎች ከየት አመጣ? ብዙ ተመራማሪዎች በተፈጥሮ ውስጥ የሚታዩት በጣም ድንቅ የሆኑ ንድፎች የተገኙት በዝግመተ ለውጥ እንደሆነና እነዚህ ንድፎች በሚሊዮን ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ በሂደት የተገኙ እንደሆኑ ይናገራሉ። ሌሎች ተመራማሪዎች የደረሱበት መደምደሚያ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ማይክል ቢሂ የተባሉ የማይክሮባዮሎጂ ባለሙያ የካቲት 7, 2005 በወጣው ዘ ኒውዮርክ ታይምስ መጽሔት ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “[በተፈጥሮ ውስጥ] የሚታየው እጅግ የተራቀቀ ንድፍ በጣም አሳማኝ የሆነ ግልጽ ማስረጃ ይሰጠናል፤ ይኸውም አንድ ነገር ዳክዬ የሚመስል እንዲሁም እንደ ዳክዬ የሚራመድና የሚጮህ ከሆነ ዳክዬ ላለመሆኑ በቂ መረጃ እስካልተገኘ ድረስ ዳክዬ ነው ብለን ለመደምደም አጥጋቢ ምክንያት አለን።” ታዲያ የእሳቸው አመለካከት ምንድን ነው? “የንድፍ መኖር በቀላሉ ሊታይ የሚችል ነገር መሆኑ ብቻ ንድፍ መኖሩን እንድንክድ ሊያደርገን አይገባም።”15

ጌኮ የተባለው እንሽላሊት ሞለኪውላዊ ኃይሎችን በመጠቀም በጣም ልሙጥ በሆነ ገጽ ላይ መጣበቅ ይችላል

ይበልጥ አስተማማኝ የሆነና ብክነትን የሚያስቀር የአውሮፕላን ክንፍ ንድፍ ያወጣ መሐንዲስ ለሥራው ተገቢው እውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ የተረጋገጠ ነው። በተመሳሳይም ይበልጥ ምቹ የሆነ ጨርቅ ወይም ይበልጥ ቆጣቢ የሆነ መኪና ለመጀመሪያ ጊዜ የሠራ ሰው ላወጣው ንድፍ እውቅና ማግኘት ይኖርበታል። እንዲያውም ለንድፍ አውጪው ተገቢውን እውቅና ሳይሰጥ የግለሰቡን ንድፍ ኮርጆ የሠራ ሰው እንደ ወንጀለኛ ይቆጠራል።

እስቲ ይህን እውነታ ቆም ብለህ አስብ፦ ከፍተኛ ሥልጠና የተሰጣቸው ተመራማሪዎች ከምሕንድስና ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት ሲሉ በተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ንድፎችን ለመኮረጅ ጥረት ያደርጋሉ። ይሁንና በተፈጥሮ ውስጥ የሚታየው የተራቀቀ ንድፍ የተገኘው የማሰብ ችሎታ ባለው አካል አማካኝነት ሳይሆን በዝግመተ ለውጥ እንደሆነ የሚናገሩ ሰዎች አሉ። ይህ አመለካከት ምክንያታዊ ይመስልሃል? በተፈጥሮ ውስጥ የሚታየውን ንድፍ አስመስሎ ለመሥራት የማሰብ ችሎታ ያለው ንድፍ አውጪ ካስፈለገ ዋናውን ለመሥራትስ የበለጠ እውቀት ያለው ንድፍ አውጪ አያስፈልግም? እንደ እውነቱ ከሆነ የበለጠ ሊመሰገን የሚገባው ዋነኛው መሐንዲስ ነው ወይስ የእሱን ንድፍ ለመኮረጅ የሚጥረው ለማጅ መሐንዲስ?

ምክንያታዊ የሆነ መደምደሚያ

በርካታ ሰዎች በተፈጥሮ ውስጥ ንድፍ እንዳለ የሚጠቁመውን ማስረጃ ከመረመሩ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ ከጻፈው ሐሳብ ጋር ተስማምተዋል፦ “የማይታዩት [የአምላክ ባሕርያት] ይኸውም ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል።”—ሮም 1:19, 20