በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሳይንስና የዘፍጥረት ዘገባ

ሳይንስና የዘፍጥረት ዘገባ

ብዙ ሰዎች ስለ ፍጥረት የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ስህተት መሆኑን ሳይንስ እንደሚያረጋግጥ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ግጭቱ ያለው በሳይንስና በመጽሐፍ ቅዱስ መካከል ሳይሆን በሳይንስና የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ ቃል በቃል መቀበል አለብን የሚል አስተሳሰብ ባላቸው ክርስቲያኖች መካከል ነው። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ፣ ሕይወት ያላቸውና ግዑዝ የሆኑ ነገሮች በሙሉ የተፈጠሩት የ24 ሰዓት ርዝመት ባላቸው ስድስት ቀናት ውስጥ እንደሆነና ይህም የተከናወነው በግምት ከ10,000 ዓመታት በፊት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጽ ይናገራሉ፤ ሆኖም ይህ አባባል ስህተት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ሰዎች የደረሱበትን ድምዳሜ አይደግፍም። መጽሐፍ ቅዱስ የእነሱን አባባል የሚደግፍ ቢሆን ኖሮ ባለፉት መቶ ዓመታት ሳይንስ የደረሰባቸው ብዙ ግኝቶች የመጽሐፉን ትክክለኝነት አጠራጣሪ ያደርጉት ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ዘገባ በጥንቃቄ ብንመረምር በማስረጃ ከተረጋገጠ ሳይንሳዊ ሐቅ ጋር እንደማይጋጭ እንገነዘባለን። በዚህም የተነሳ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ስድስቱ የፍጥረት ቀናት እያንዳንዳቸው የ24 ሰዓት ርዝመት እንዳላቸው በሚያምኑ ክርስቲያኖች ሐሳብ አይስማሙም። እስቲ ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንመልከት።

የዘፍጥረት መጽሐፍ ምድርና መላው ጽንፈ ዓለም የ24 ሰዓት ርዝመት ባላቸው ስድስት ቀናት ውስጥ ከጥቂት ሺህ ዓመታት በፊት እንደተፈጠሩ አያስተምርም

“በመጀመሪያ” የተባለው የትኛው ጊዜ ነው?

የዘፍጥረት ዘገባ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” በሚለው ትልቅ ትርጉም ባለው ሐሳብ ይጀምራል። (ዘፍጥረት 1:1) ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን፣ በዚህ ዓረፍተ ነገር ላይ የተጠቀሰው ክንውን ከቁጥር 3 ጀምሮ በተገለጹት የፍጥረት ቀናት ውስጥ እንደማይካተት ይስማማሉ። ይህ ደግሞ ትልቅ ትርጉም አለው። ከመጽሐፍ ቅዱስ የመክፈቻ ቃላት መረዳት እንደሚቻለው የእኛን ፕላኔት ምድርን ጨምሮ መላው ጽንፈ ዓለም የፍጥረት ቀናት ከመጀመራቸው በፊት በውል ለማይታወቅ ረጅም ዘመን ኖሯል።

የሥነ ምድር ተመራማሪዎች ምድር 4 ቢሊዮን ዓመት የሚያህል ዕድሜ እንዳላት ሲገምቱ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ደግሞ ጽንፈ ዓለም እስከ 15 ቢሊዮን ዓመት የሚደርስ ዕድሜ እንዳለው አስልተዋል። ታዲያ እነዚህ ግኝቶችም ሆኑ በዚህ ረገድ ወደፊት የሚደረጉ ማሻሻያዎች ከዘፍጥረት 1:1 ጋር ይጋጫሉ? በፍጹም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የሰማያትና የምድር’ ትክክለኛ ዕድሜ ምን ያህል እንደሆነ አይገልጽም። በመሆኑም ሳይንስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጋር አይጋጭም።

የፍጥረት ቀናት ምን ያህል ርዝመት አላቸው?

ስለ ፍጥረት ቀናት ርዝመትስ ምን ሊባል ይችላል? ቃል በቃል የ24 ሰዓት ርዝማኔ ነበራቸው? አንዳንዶች የዘፍጥረት መጽሐፍ ጸሐፊ የሆነው ሙሴ፣ ከስድስቱ የፍጥረት ቀናት በኋላ ያለው ቀን ለሳምንታዊው ሰንበት ምሳሌ እንደሆነ ከጊዜ በኋላ ስለገለጸ እያንዳንዱ የፍጥረት ቀን ቃል በቃል የ24 ሰዓት ርዝመት ያለው መሆን አለበት ይላሉ። (ዘፀአት 20:11) ታዲያ የዘፍጥረት ዘገባ ይህን ሐሳብ ይደግፋል?

በፍጹም አይደግፍም። “ቀን” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል 24 ሰዓትን ብቻ ሳይሆን የተለያየ ርዝመት ያለውን ጊዜ ሊያመለክት ይችላል። ለምሳሌ ሙሴ፣ የአምላክን የፍጥረት ሥራዎች ጠቅለል አድርጎ በሚገልጽበት ጊዜ ስድስቱንም የፍጥረት ቀናት እንደ አንድ ቀን ገልጿቸዋል። (ዘፍጥረት 2:4 የ1954 ትርጉም) በተጨማሪም በመጀመሪያው የፍጥረት ቀን ላይ አምላክ “ብርሃኑን ‘ቀን’፣ ጨለማውን ‘ሌሊት’” ብሎ ጠርቶታል። (ዘፍጥረት 1:5) እዚህ ላይ “ቀን” የተባለው ከ24 ሰዓት ውስጥ ከፊሉ ጊዜ ብቻ ነው። በእርግጥም እያንዳንዱ የፍጥረት ቀን የ24 ሰዓት ርዝመት አለው ብሎ ለመደምደም የሚያስችል ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት የለም።

ታዲያ የፍጥረት ቀናት ምን ያህል ርዝመት አላቸው? መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አይናገርም፤ ይሁን እንጂ በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 እና 2 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው የፍጥረት ቀናት ረጅም ዘመናትን ያመለክታሉ።

ስድስት የፍጥረት ቀናት

ሙሴ ዘገባውን የጻፈው በዕብራይስጥ ሲሆን ታሪኩን ያቀረበው ምድር ላይ ካለ ሰው እይታ አንጻር ነው። እነዚህ ሁለት ነጥቦችና የፍጥረት ቀናት ከመጀመራቸው በፊት ጽንፈ ዓለም እንደነበረ ያገኘነው እውቀት አንድ ላይ ሲጣመሩ ከፍጥረት ዘገባ ጋር በተያያዘ የሚነሱትን አብዛኞቹን ውዝግቦች ለማስወገድ ይረዱናል። እንዴት?

በአንድ የፍጥረት “ቀን” የተጀመሩ ክንውኖች ከዚያ በኋላ ባለው ቀን ወይም ‘ቀናት’ ቀጥለው ነበር

የዘፍጥረትን ዘገባ በጥንቃቄ ከመረመርን በአንድ የፍጥረት “ቀን” የተጀመሩ ክንውኖች ከዚያ በኋላ ባለው ቀን ወይም ‘ቀናት’ እንደቀጠሉ እንገነዘባለን። ለምሳሌ፣ ቀድሞውንም ከነበረችው ፀሐይ የሚመጣው ብርሃን የመጀመሪያው የፍጥረት “ቀን” ከመጀመሩ በፊት ወደ ምድር ገጽ መድረስ አይችልም ነበር፤ ይህ የሆነው ጥቅጥቅ ባለ ደመና ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። (ኢዮብ 38:9) እንደ ግርዶሽ የሆነው ይህ ነገር በመጀመሪያው “ቀን” መገፈፍ በመጀመሩ ደብዘዝ ያለ ብርሃን የምድርን ከባቢ አየር ዘልቆ መግባት ጀመረ። *

በሁለተኛው “ቀን” ከባቢ አየሩ እየጠራ የሄደ ይመስላል፤ ይህም ጥቅጥቅ ባለው ደመናና ከታች ባለው ውቅያኖስ መካከል ክፍተት እንዲፈጠር አደረገ። በአራተኛው “ቀን” ከባቢ አየሩ ይበልጥ እየጠራ ስለሄደ ፀሐይና ጨረቃ “በሰማይ” ላይ ግልጽ ሆነው መታየት ጀመሩ። (ዘፍጥረት 1:14-16) በሌላ አነጋገር ምድር ላይ ካለ ሰው እይታ አንጻር ፀሐይና ጨረቃ መታየት ቻሉ። እነዚህ ክንውኖች የተፈጸሙት ቀስ በቀስ ነው።

በተጨማሪም የዘፍጥረት ዘገባ ስስ ክንፍ ያላቸውንና (membrane-winged) ሌሎች ነፍሳትን ጨምሮ በራሪ ፍጥረታት በአምስተኛው “ቀን” መታየት እንደጀመሩ ይገልጻል።

መጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀመበት አገላለጽ በእያንዳንዱ የፍጥረት ቀን ከተከናወኑት ዐበይት ክንውኖች አንዳንዶቹ የተፈጸሙት በቅጽበት ሳይሆን ቀስ በቀስ ሊሆን እንደሚችል ያመለክታል፤ ምናልባትም አንዳንዶቹ ክንውኖች በቀጣዮቹ የፍጥረት ቀናት ቀጥለው ሳይሆኑ አይቀሩም። *

እንደየወገናቸው

ታዲያ ዕፅዋትና እንስሳት በዚህ መንገድ ደረጃ በደረጃ ወደ ሕልውና መምጣታቸው አምላክ ዓይነታቸው ቁጥር ስፍር የሌለውን ሕያዋን ፍጥረታት ለማስገኘት በዝግመተ ለውጥ እንደተጠቀመ ያሳያል? በፍጹም። አምላክ ዋና ዋናዎቹን የዕፅዋትና የእንስሳት ‘ወገኖች’ በሙሉ እንደፈጠረ ታሪኩ በግልጽ ያመለክታል። (ዘፍጥረት 1:11, 12, 20-25) ታዲያ እነዚህ የመጀመሪያ የዕፅዋትና የእንስሳት ‘ወገኖች’ ሲፈጠሩ፣ የአካባቢያቸው ሁኔታ በሚለወጥበት ጊዜ ራሳቸውን ከለውጡ ጋር የማላመድ ችሎታ ተሰጥቷቸው ነበር? የአንድ “ወገን” ድንበር የሚባለው ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምንም አይናገርም። ሕይወት ያላቸው ነገሮች ‘እንደየወገናቸው ይርመሰመሱ እንደነበር’ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 1:21) ይህ መግለጫ በአንድ “ወገን” ውስጥ ሊፈጠር የሚችለው የዓይነት መብዛት ገደብ እንዳለው ያመለክታል። ዋና ዋናዎቹ የዕፅዋትና የእንስሳት ወገኖች በረጅም ዓመታት ውስጥ እምብዛም እንዳልተለወጡ ቅሪተ አካላትም ሆኑ ዘመናዊ ምርምር ያረጋግጣሉ።

ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ የሚራቡት “እንደየወገናቸው” መሆኑ በዘመናዊ ምርምር ተረጋግጧል

የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ ቃል በቃል መቀበል አለብን የሚሉ ሰዎች ከሚናገሩት በተቃራኒ ምድርንና በላይዋ ያሉትን ሕያዋን ፍጥረታት ጨምሮ ጽንፈ ዓለም በአጠቃላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በቅርብ ዘመን እንደተፈጠረ የዘፍጥረት መጽሐፍ አያስተምርም። ከዚህ ይልቅ ስለ ጽንፈ ዓለም አፈጣጠርና በምድር ላይ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ወደ ሕልውና ስለመጡበት መንገድ የሚገልጸው የዘፍጥረት ዘገባ በቅርብ ጊዜ ከተደረሰባቸው የሳይንስ ግኝቶች ጋር ይስማማል።

ብዙ የሳይንስ ሊቃውንት በፍልስፍና ላይ በተመሠረተው እምነታቸው ምክንያት፣ አምላክ ሁሉንም ነገሮች እንደፈጠረ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ አይቀበሉም። የሚገርመው ግን ሙሴ፣ ጥንታዊ በሆነውና ዘፍጥረት በተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ጽንፈ ዓለም መጀመሪያ እንዳለው እንዲሁም በምድር ላይ ሕይወት መታየት የጀመረው በጊዜ ሂደት፣ ደረጃ በደረጃ እንደሆነና ይህም በረጅም ጊዜ ውስጥ እንደተከናወነ ጽፏል። ሙሴ ከ3,500 ዓመታት በፊት እንዲህ ያለውን ከሳይንስ አንጻር ትክክለኛ የሆነ መረጃ ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነው? ምክንያታዊ የሚሆነው መልስ አንድ ነው፤ ሰማያትንና ምድርን ለመፍጠር የሚያስችል ኃይልና ጥበብ ያለው አካል እንዲህ ያለውን የመጠቀ እውቀት ለሙሴ መስጠት እንደሚችል አያጠራጥርም። ይህም፣ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ “በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ” መሆኑን የሚናገረው ሐሳብ እውነት መሆኑን ያረጋግጣል። *2 ጢሞቴዎስ 3:16

ይሁንና ‘ስለ ፍጥረት የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ማመን ወይም አለማመን ለውጥ ያመጣል? ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። የምታምነው ነገር ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል የሚያሳዩ አንዳንድ አሳማኝ ምክንያቶችን እንመልከት።

^ አን.13 በመጀመሪያው “ቀን” ላይ ስለተከናወነው ነገር ሲገለጽ ብርሃንን ለማመልከት የተሠራበት ኦር የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን ቃሉ ብርሃንን በአጠቃላይ ያመለክታል፤ በአራተኛው “ቀን” ላይ የተጠቀሰው ቃል ግን ማኦር ሲሆን ይህ ቃል ብርሃኑ የተገኘበትን ምንጭ ያመለክታል።

^ አን.16 ለምሳሌ በስድስተኛው የፍጥረት ቀን አምላክ የሰው ልጆችን “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት” ብሏቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28, 31) ይህ ክንውን፣ እንኳን በዚያ ቀን ሊፈጸም እስከ ቀጣዩ “ቀን” ድረስ ገና አልጀመረም ነበር።—ዘፍጥረት 2:2

^ አን.20 በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የመጣ መሆኑን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? የተባለውን jw.org/am ላይ የሚገኝ ቪዲዮ ተመልከት።